ቀጥታ፡

በዞኑ ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ስርዓትን በማስፈን የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው

ደብረ ማርቆስ ፤ ሰኔ 12/2018 (ኢዜአ)፦ በምስራቅ ጎጃም ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ስርዓትን በማስፈን የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ መሬት መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ፈንታሁን ብርሃን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ስርዓትን በማስፈን የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ርብርብ እየተደረገ ነው።


 

በዚህም ባለፉት ዓመታት ለሁሉም አርሶ አደሮች ጊዜያዊ የመሬት ባለቤትነት ማስረጃ የመስጠት ሁኔታ እንደነበር ገልጸው ዘንድሮ ይህንን ወደ ቋሚ ይዞታ ማረጋገጫ በማሳደግ የባለቤትነት መብታቸውን ለማረጋገጥ በትኩረት መሰራቱን ገልጸዋል።

እስካሁን በተደረገው ጥረትም ከ600 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች በካርታ የተደገፈ ቋሚ የመሬት ባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር በማሰራት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

ቋሚ የመሬት ማረጋገጫ ካገኙት አርሶ አደሮች ከ3 ሺህ 586 በላይ ለሚሆኑት ከ130 ሚሊዮን ብር በላይ የባንክ ብድር አግኝተው በሌሎች የገቢ ማስገኛ ዘርፎች ለመሰማራት እድል እንደተፈጠረላቸው አብራርተዋል።

በተጨማሪም ዋስትና በማግኘታቸው የእርሻ ማሳቸውን ለምነት በመጨመር ዘላቂ ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ያለፈ ምርት ለማምረት መነሳሳትን ፈጥሮላቸዋል።

ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ቀሪ አርሶ አደሮችን በካርታ የተደገፈ ቋሚ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ተጠቃሚ ለማድረግም በየደረጃው ያለው አመራርና ባለሙያ ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል።


 

በዞኑ የእናርጅ እናውጋ ወረዳ የፈለገ ብርሃን ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ማማሩ ወርቅነህ እንደገለጹት፤ ቋሚ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ማግኘታቸው ከወሰን ማስከበር ጋር የነበረባቸውን ችግር እንዳስቀረላቸው ተናግረዋል።

የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ደረጀ አጥናፉ በበኩላቸው፤ ቋሚ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ በማሰራታቸው በመሬታቸው ላይ ሙሉ የባለቤትነት ስሜት እንዲያዳብሩ እንዳደረጋቸው አስረድተዋል።

በቀጣይም ደብተሩን አስይዘው በመበደር ከሰብል ልማት በተጨማሪ በሌሎች የገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ ለመሰማራት አቅደው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም