ቀጥታ፡

በምዕራብ ጎንደር ዞን በጽንፈኞች ላይ የተጠናከረ እርምጃ በመውሰድ በአካባቢው ሰላም ማስፈን ተችሏል

ገንዳውኃ፤ ሰኔ 12/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን በጽንፈኞች ላይ የተጠናከረ እርምጃ በመውሰድ በአካባቢው ሰላም ማስፈን መቻሉን የዞኑ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ገለጸ።

በዞኑ የጽንፈኞችን አኩይ አላማ በማክሸፍ ለዘላቂ ሰላምና ልማት በመትጋት የአካባቢው ህብረተሰብ ከጸጥታ አካላት ጎን በመሰለፍ የነቃ ትብብርና ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን መምሪያው አስታውቋል።

በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ እገታና ዘረፋ የሚፈፅመው ጽንፈኛ ቡድን በሚገኘው አጋጣሚ ማህበራዊ ተቋማትን በማውደም የህዝብ ጠላት መሆኑን በተግባር አሳይቷል።

የተለያዩ የህዝብና የመንግስት አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማቶችን በማውደም፣ ሰዎችን በማገትና በመዝረፍም ይታወቃል።

በመሆኑም ይህንን ጽንፈኛ ቡድን በመታገል ህግ ማስከበር ለጸጥታ አካላት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ የምዕራብ ጎንደር ዞንና አካባቢው ነዋሪዎች ከጸጥታ ሃይሉ ጎን በመሰለፍ የሰላማቸው ዘብ ሆነው እየሰሩ መሆኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ሃላፊ ደረሰ አዱኛ ገልጸዋል።

የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ለማስተጓጎል ጽንፈኛ ቡድኑ የተለያዩ ጥረቶችን ቢያደርግም ህዝቡ በራሱ ተነሳሽነት ከማለዳ እስከ ምሽት ድምፁን በመስጠት ለሰላም ያለውን ጽኑ አቋም አሳይቷል ብለዋል።

በዚህም በምዕራብ ጎንደር ዞን በጽንፈኞች ላይ የተጠናከረ እርምጃ በመውሰድ በአካባቢው ሰላም ማስፈን የተቻለ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎችም የማህበረሰብ ክፍሎች ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር በማሳየት ጽንፈኛ ቡድኑ የመንግስትን የሰላም አማራጭ እንዲቀበል የበኩላቸውን ጥረት ማድረጋቸውንም አንስተዋል።

በዚህም በርካታ ታጣቂዎች የሰላም ጥሪውን ተቀብለው በመግባት ማህበረሰቡን መቀላቀላቸውን ገልጸው የቀሩትም እንዲገቡ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

ለሰላም የሚደረገው ጥረት እንዳለ ሆኖ ከዚህ በተቃራኒ በጥፋታቸው የሚቀጥሉ ካሉ የተጠናከረ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ሃላፊው አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም