ቀጥታ፡

ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተተከሉ ችግኞች ተጠቃሚ ሆነናል - አርሶ አደሮች

ቴፒ፤ ሰኔ 12/2018 (ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተተከሉ ችግኞች ተጠቃሚ መሆናቸውን በሸካ ዞን የየኪ ወረዳ አርሶአደሮች ገለጹ።

አርሶአደሮቹ በወረዳው "አላሞ" በሚባለውና በቆላማነቱ በሚታወቀው አካባቢ ቀደም ሲል የተተከሉ ችግኞች የአካባቢውን ስነምህዳር ወደ ወይናደጋ እንዲቀየር ያደረጉ ሲሆን በፍራፍሬ ምርትም ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

ኢዜአ ካነጋገራቸው የወረዳው ነዋሪዎች መካከል አቶ አይንአዲስ ገበየሁ እንዳሉት፤ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተተከሉ የግራቪላ ዛፎች ሥር ቁንዶ በርበሬ በማልማት ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል።

በቆላማ አካባቢ አቮካዶ እና ሌሎች የፍራፍሬ ችግኞችን በመትከል የአካባቢውን ሥነ ምህዳር ከመጠበቅ ባለፈ ከምርቱም ገቢያቸውን  እያሳደጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

የአረንጓዴ አሻራ ልማት ኢኒሼቲቭ ከተጀመረ ወዲህ በማሳቸው የችግኝ ዘር አዘጋጅተውና ለሌሎች አርሶ አደሮች በሽያጭ በማቅረብ ገቢያቸውን እያሰፉ እንደመጡም አክለዋል።

ምርጥ የቡና ዘር እና ለቡና ጥላ የሚሆኑ ችግኞችን በማሳቸው አዘጋጅተው ለውጤት እንዳበቁ የተናገሩት ደግሞ ሌላው የወረዳው ነዋሪ አቶ ኃይሌ መንግስቴ ናቸው።

ከቡና በተጨማሪ በጓሯቸው ሙዝና ብርቱካን ተክለው ጥሩ ምርት ለማግኘት በመንከባከብ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አምና ከቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል የወሰዳቸውንና ፈጥኖ ምርት የሚሰጡ የፓፓያ፣ ማንጎና ሙዝ እንዲሁም እንደ ካካዎ ያሉ የቅመማ ቅመም ችግኞችን ተክሎ ጥሩ ውጤት ማየቱን የገለጸው ደግሞ ወጣት አማረ ብርሃኑ ነው።

እንደወጣቱ ገለጻ በዘንድሮ ክረምትም ተጨማሪ ችግኝ በመትከል አካባቢውን ለመጠበቅና ከውጤቱም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።

ሌላው አርሶ አደር ጢሞቴዎስ ከሮ በበኩላቸው፤ ከዚህ በፊት ዘርፈ ብዙ ጥቅም ካላቸው ችግኞች መካከል ዋንዛ፣ ቁንዶ በርበሬ እና ቡናን ተክለው በውጤቱ ጥቅም እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል። 


 

ቀደም ሲል በተተከሉ ችግኞች በአካባቢው የአየር ፀባይ ላይ ለውጥ ማየታቸውን የገለጹት አርሶ አደሩ፣ በዚህም ዘንድሮ ዝናብ በበቂ ሁኔታ እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የየኪ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ባለሙያ አቶ ፍስሐ ግዛው፤ በወረዳው ካሉ አካባቢዎች መካከል አላሞ በረሃማ እንደነበር አስታውሰው፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ተከትሎ አካባቢው ደን መልበሱንና የአየር ጸባዩም እየተስተካከለ መምጣቱን አረጋግጠዋል።


 

በአካባቢው የተተከሉ ችግኞች ደን ከመሆን ባሻገር በፍራፍሬ እና በቅመማ ቅመም ከፍተኛ ምርት እያስገኙ በመሆኑ የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት እያደገ መጥቷል ብለዋል።

እንደባለሙያው ገለጻ፣ ቀደም ሲል በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ከተተከሉ ችግኞች የተገኘ የፍራፍሬ ምርት ከአካባቢ አልፎ ለማዕከላዊ ገበያ እየቀረበ ነው።

ለዘንድሮው የክረምት አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርም ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸው ችግኞች መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም