ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን እና አካባቢው በጽንፈኞች ላይ በተወሰደ እርምጃ አስተማማኝ ሰላም ማስፈን ተችሏል

ባህር ዳር፤ ሰኔ 12/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን እና አካባቢው በጸጥታ ሃይሉና በህብረተሰቡ ጠንካራ ትብብር በጽንፈኞች ላይ በተወሰደ እርምጃ አስተማማኝ ሰላም መስፈኑን የዞኑ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ አስታወቀ።

በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በባንዳነት የተሰለፈው ጽንፈኛ ቡድን መሰረተ ልማቶችን በማውደም፣ ሰዎችን በማገትና በመዝረፍ ጥፋቶችን ሲፈጽም ቆይቷል።

በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ማህበራዊ አገልግሎትና የልማት ስራዎች እንዲስተጓጎሉ በተለይም ደግሞ የትምህርትና የጤና ተቋማት እንዲወድሙ ጽንፈኛ ቡድኑ ብዙ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱም ተመላክቷል።

የሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ለማስተጓጎልም የተለያዩ ጥረቶች ቢያደርግም ህዝቡ ከማለዳ እስከ ምሽት ድምፁን በመስጠት ለሰላም ያለውን ጽኑ አቋምና ቁርጠኝነት በተግባር አሳይቷል።

በክልሉ ሰሜን ጎጃም ዞን እና አካባቢው ያለውን ወቅታዊ የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው የዞኑ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ሃላፊ ገብረሥላሴ ታዘብ፤ ህዝቡ ጽንፈኞችን አምርሮ በመጥላትና በመታገል ሰላሙን እያስከበረ ይገኛል ብለዋል።

የዞኑ ህዝብ በተለያዩ አጋጣሚዎች ጽንፈኞችን በማውገዝ የመንግስትን የሰላም ጥሪ እንዲቀበሉ ጥረት ማድረጉን አስታውሰው በዚህም ሰላምን መርጠው ህብረተሰቡን የተቀላቀሉ መኖራቸውን ተናግረዋል።

መንግስትም የማቋቋሚያ በጀት በመመደብ ወደ ስራ ገብተው የበደሉትን ህዝብ በልማት እንዲክሱ አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን አንስተዋል።

ከዚህ በተቃራኒ የህዝብ ሃብትና ንብረቶችን በመዝረፍና በማውደም እንዲሁም በእገታ የወንጀል ድርጊታቸው የቀጠሉትን በመከታተል እርምጃ እንዲወሰድባቸው መደረጉን ገልጸዋል።

በዞኑና አካባቢው በጸጥታ ሃይሉና በህብረተሰቡ ጠንካራ ትብብር በጽንፈኞች ላይ በተወሰደ እርምጃ አሁን ላይ አስተማማኝ ሰላም ማስፈን መቻሉን ሃላፊው ተናግረዋል።

የአመራሩ፣ የህብረተሰቡና የጸጥታ ሃይሉ ለሰላም እያደረጉት ያለው ጠንካራ ትብብርና ቅንጅታዊ ጥረት ሰላምን እያጸና ይገኛል ብለዋል።

አሁንም በጫካ የሚገኙ አካላት የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል የሰላም ዘብና የልማት አርበኛ ለመሆን እንዲመለሱ አቶ ገብረሥላሴ መክረዋል።

ከጥፋታቸው በማይመለሱ ጽንፎኞች ላይ የህግ ማስከበር ስራውን አጠናክሮ በማስቀጠል የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም