የምክክር ሂደቱን በስኬት በማጠናቀቅ የጋራና አሰባሳቢ ትርክት መገንባትና ኢትዮጵያን ማፅናት የዜጎች ሁሉ አደራና ሃላፊነት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የምክክር ሂደቱን በስኬት በማጠናቀቅ የጋራና አሰባሳቢ ትርክት መገንባትና ኢትዮጵያን ማፅናት የዜጎች ሁሉ አደራና ሃላፊነት ነው
ወልቂጤ፤ ሰኔ 12/2018(ኢዜአ)፦ የምክክር ሂደቱን በስኬት በማጠናቀቅ የጋራና አሰባሳቢ ትርክት መገንባትና ኢትዮጵያን ማፅናት የዜጎች ሁሉ አደራና ሃላፊነት መሆኑን ምሁራን ገለጹ።
ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ላለፉት አራት አመታት አካታች፣ አሳታፊና ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ በውጤታማነት መካሄዱን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታውቋል።
በመቀጠልም ዋናውን የምክክር ጉባኤ በሀምሌ ወር በአዲስ አበባ ለማካሄድ የተሟላ ዝግጅት መደረጉ ታውቋል።
የምክክር ሂደቱንና የመጨረሻ ውጤቱን ስኬታማ ከማድረግ አንፃር አጠቃላይ ከዜጎች ምን ይጠበቃል ሲል ኢዜአ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንን አነጋግሯል።
የምክክር ሂደቱ ቀጥሎ ዋናው የምክክር ጉባኤ በስኬት እንዲቋጭ የኮሚሽኑን ብርቱ ጥረት በማገዝ የዜጎች ጠንካራ ተሳትፎ፣ ድጋፍና ትብብር አስፈላጊ መሆኑን ምሁራኑ አንስተዋል።
በሀዋሳ ዩንቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ፈቀደ ምኑታ(ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ባለፉት አራት ዓመታት በህዝብ የተሰጠውን ታሪካዊ ሃላፊነት ለመወጣት ያደረገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
የምክክር ሂደቱ አካታች፣ አሳታፊና ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ መካሄዱን በብዙ መልኩ መረዳት መቻላቸውን ጠቁመው፤ በስኬት እንዲጠናቀቅ የማድረግ ጥረት ከሁላችንም ይጠበቃል ብለዋል።
የኢትዮጵያን የቆዩ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ከምክክር የበለጠ አማራጭ አለመኖሩን አንስተው ይህንን እድል በአግባቡ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።
በመሆኑም የምክክር ሂደቱን በስኬት በማጠናቀቅ የጋራና አሰባሳቢ ትርክት በመገንባት ኢትዮጵያን ማፅናት የሁላችንም አደራና ሃላፊነት ነው ብለዋል።
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ በላይ ዘርጋ (ዶ/ር)፤ ለሀገረ መንግስት ግንባታ፣ ዘላቂ ሰላምና ልማት አሁን ላይ በፅኑ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
የምክክሩ ኮሚሽኑን ብርቱ ጥረት በማገዝ ዋናውን የምክክር ጉባኤ በማካሄድና ችገሮችን በዘላቂነት በመፍታት ኢትዮጵያን ለዜጎቿ ሁሉ የምትመች ሀገር ማድርግ አለብን ነው ያሉት።
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ አለማየሁ ስፍር(ዶ/ር)፤ ምክክሩ ጠንካራ ሀገረመንግስት ለመገንባትና ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል።
የዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ጀምሮ በአዲስ አበባ የሚካሄድ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መግለጹ ይታወሳል።