ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ያላትን ግንኙነት በማጎልበት ዓለም አቀፋዊ ተደማጭነቷን ማሳደግ ችላለች

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 12/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ያላትን ግንኙነት በማጎልበት ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የዲፕሎማሲ ተደማጭነቷን ማሳደግ መቻሏን የዘርፉ ምሁራን ገለፁ።

በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕግና ገቨርናንስ ኮሌጅ ዲን ደብረወርቅ ደበበ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የዲፕሎማሲና ጠንካራ የውጭ ግንኙነት ታሪክ ያላት ሀገር ናት።

ከለውጡ ወዲህ የዲፕሎማሲ እመርታ እየተመዘገበ መሆኑን ጠቅሰው፥ የመንግስት ለመንግስትና የመሪዎች ግንኙነት ማደጉ የበርካታ ሀገራት መሪዎች ለይፋዊ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ማስቻሉን ገልጸዋል።


 

ሀገሪቱ በአፍሪካና ዓለም አቀፍ ተቋማት ያላት ውክልና እያደገ መምጣቱ እንዲሁም ከሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት ጥቅሞቿነ በሚያስከብሩ ትብብሮች እየተጠናከረ መሆኑን ገልፀዋል።

አዲስ አበባም በርካታ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ጉባኤዎችን ማስተናገዷ፥ የዲፕሎማሲና የልማት ለውጦችን የሚመሰክር፣ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተፅዕኖ የሚያሳይና በዘርፉ ተሞክሮ እንዳላት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዳንኤል ሀንድኖ (ዶ/ር) በበኩላቸው የኢትዮጵያ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ግንኙነት ማደግ የሀገሪቱ የዲፕሎማሲ አቅምና ቁመና እንዲሁም ተፅዕኖ ፈጣሪነት እያደገ መምጣቱን ያሳያል ነው ያሉት።


 

የተለያዩ ሀገራትና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች በኢትዮጵያ ያደረጉት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ሀገሪቱ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በፖለቲካ እድገት ማስመዝገቧንና ተፅዕኖ መፍጠሯን የሚያሳይ እንደሆነም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስከብር እንደሆነም ነው የተናገሩት።

የውጭ ግንኙነት ከሚመራባቸው ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ የውስጥ ጥንካሬ መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ጠንካራ ውስጣዊ አቅም መፍጠሯ ከሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት እንዲጠናከር ማስቻሉን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የምትገኝበት ስትራቴጂካዊና ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ለውጭ ግንኙነት አስተዋፅኦ የሚያበረክት መሆኑንም ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ በመሪዎቿ በኩል የምታደርገው ግንኙነት መጠናከር የውጭ ደጋፊ ኃይሎችን በማሳደግ የሀገሪቱ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ተሳትፎን በማሳደግ ተደማጭነቷ እንዲጨምር እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም