በምስራቅ ጎጃም ዞን በበጀት ዓመቱ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የጠጠር መንገዶችና ድልድዮች ለአገልግሎት በቅተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ጎጃም ዞን በበጀት ዓመቱ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የጠጠር መንገዶችና ድልድዮች ለአገልግሎት በቅተዋል
ደብረ ማርቆስ ፤ ሰኔ 12/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን በበጀት ዓመቱ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የጠጠር መንገዶችና ድልድዮች ለአገልግሎት መብቃታቸውን የዞኑ መንገድ፣ ትራንስፖርትና ሎጅስቲክ መምሪያ አስታወቀ።
የምስራቅ ጎጃም ዞን በግብርና ምርታማነትና በከብት እርባታ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ካላቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች አንዱ ነው።
ይሁን እንጂ በተለይም በክረምት ወቅት የሚስተዋለው የጭቃና የመንገድ መበላሸት ችግር፣ አርሶ አደሩ ምርቱን በወቅቱ ወደ ገበያ እንዳያቀርብ ትልቅ ማነቆ ሆኖ ቆይቷል።
በክልሉ መንግስትና የዞኑ አስተዳደር ይህንን የመሰረተ-ልማት ክፍተት ለመሙላትና የገጠር-ከተማ ትስስርን ለማጠናከር በበጀት ዓመቱ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣባቸው የጠጠር መንገዶች ተገንብተዋል፡፡
የዞኑ መንገድ፣ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ መምሪያ ሃላፊ አቶ ማናየ አዳነ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታው የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስተጋብር እያሳደገው ይገኛል።
ከመንግስትና ከማህበረሰቡ በተገኘ 300 ሚሊዮን ብር ወጪ የጠጠር መንገዶች መገንባታቸውን ጠቁመው፤ ከዚህም ውስጥ ከ72 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመተው ከማህበረሰቡ የተገኘ ነው ብለዋል።
በዚህም 60 ኪሎ ሜትር አዲስ የጠጠር መንገድ ግንባታ፣ ከአንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ነባር መንገድ ጥገናና ሶስት ተጠልጣይ ድልድዮች እንዲሁም የኮንክሪት ድልድይ መገንባት መቻሉን ተናግረዋል።
ለመንገድ ግንባታና ጥገናውም ማህበረሰቡ በገንዘብ፣ በጉልበቱና በቁሳቁስ የላቀ አስተዋጽኦ በማበርከቱ የተሳካ ስራ እንዲሰራ ማስቻሉን አንስተዋል።
በጎዛምን፣ አዋበል፣ እናርጅ፣ የጁቤ፣ ደብረ ኤልያስን ጨምሮ በስምንት ወረዳዎች የተከናወነው የመንገድና ድልድይ ግንባታ 325 የገጠር ቀበሌዎችን እርስ በእርስ ለማገናኘት ያስችላል ብለዋል።
የመንገድና ድልድይ ግንባታው የዞኑ ህዝብ እስካሁን በእንስሳትና በሸክም ሲያጓጉዝ የነበረውን ሸቀጥና የግብርና ግብአት በመኪና በማጓጓዝ ፈጥኖ ለልማት ስራው እንዲደርስ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።
በዞኑ ጎዛምን ወረዳ የለቅለቂታ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ይግዛው አየለ እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ የተገነባላቸው የጠጠር መንገድ የግብርና ምርታቸውን ወደ ገበያ ለማቅረብና የግብርና ግብዓትን ለማጓጓዝ አስችሏቸዋል።