የአሜሪካ የቪዛ ዕገዳ በሰሜን ኢትዮጵያ ለተፈጠረው ውጥረት የጽንፈኛው የህወሃት ቡድንን ተጠያቂ ያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአሜሪካ የቪዛ ዕገዳ በሰሜን ኢትዮጵያ ለተፈጠረው ውጥረት የጽንፈኛው የህወሃት ቡድንን ተጠያቂ ያደረገ ነው
አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 11/2018 (ኢዜአ)፡- በሕወሃት ጽንፈኛ አመራሮች እና ቤተሰቦቻቸው ላይ የተጣለው የአሜሪካ የቪዛ እገዳ በሰሜን ኢትዮጵያ ላለው ውጥረት መባባስ ቀጥተኛ ተጠያቂ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው ሲሉ የቀድሞው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ገለጹ።
አቶ ጌታቸው ረዳ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሰጡት ማብራሪያ እገዳው ከዚህ የጥፋት ቡድን ጋር በጥቅምም ሆነ በስትራቴጂ ይተባበራሉ ተብለው ለሚጠረጠሩ እንደ ሻቢያው መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ መንግስት ላሉ የውጭ አካላትም የተላለፈ ግልጽ ማስጠንቀቂያ ነው።
የእርምጃው ትልቅነት በቪዛ መከልከሉ ላይ አይደለም፤ ይልቁንም ዋሽንግተን በኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጠረው አዲስ ውጥረት ተጠያቂነቱን ሙሉ በሙሉ በደብረጽዮን ገብረሚካኤል በሚመራው ቡድን ላይ ማድረጉ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ ጌታቸው ይህንኑ እርምጃ ሲያብራሩ የቪዛ እገዳው በተለይ ከደብረጽዮን ጋር በቅርብ የሚሰሩ እና በትግራይ ክልል ለሚታየው ቀውስ መባባስ ምክንያት የሆኑ የሕወሃት አክራሪ አባላትን ለይቶ ያነጣጠረ መሆኑንም ገልጸዋል።
አሜሪካ በኢትዮጵያ ሰላምን ለማደፍረስ እና ግጭት ለመቀስቀስ እየተንቀሳቀሱ በሚገኙ የቀድሞ የህወሓት ጽንፈኛ አመራሮች እና በቅርብ የቤተሰብ አባሎቻቸው ላይ የቪዛ እገዳ መጣሏን አስታውቃለች።
የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ማዕቀቡ የተጣለው በኢሚግሬሽንና ዜግነት ሕግ አንቀጽ 212(a)(3)(C) በተሰጣቸው ሥልጣን መሠረት መሆኑንም ገልጸዋል።
ይህ የቪዛ እገዳ በትግራይ ክልል ያለውን ቀውስ ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶችን በሚያደናቅፉ፣ ሰላምን በሚያናጉ የሕወሃት ጽንፈኛ አባላትና የቅርብ የቤተሰብ አባሎቻቸው ላይ ያነጣጠረ ነው።
አሜሪካ በሰላምና በክብር መኖር የሚፈልገውን የትግራይ ክልል ሕዝብን ጨምሮ ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን እንደምትቆም አስታውቃለች።
በቀጣናው ሰላምና መረጋጋትን አደጋ ላይ የሚጥሉ የሕወሃት ባለሥልጣናትንና ሌሎች ግለሰቦችን ድርጊት ለማጋለጥ እንዲሁም ተጠያቂነትን ለማስፈን ዋሽንግተን ያሏትን ዲፕሎማሲያዊ አማራጮች በሙሉ መጠቀሟን እንደምትገፋበትም ገልጻለች።