በፌዴራል ዋና ኦዲተር የኦዲት ሽፋን፣ ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳደግ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች የሚበረታቱ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በፌዴራል ዋና ኦዲተር የኦዲት ሽፋን፣ ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳደግ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች የሚበረታቱ ናቸው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2018 (ኢዜአ):- የፌዴራል ዋና ኦዲተር የኦዲት ሽፋንን ጥራትና ተደራሽነት ለማሳደግ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን የሕዝብ ተወካዮች የምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ ገለጹ።
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን በ26ኛ መደበኛ ስብሰባው፤ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ያቀረበውን የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የ2017 በጀት ዓመት የፋይናንሺያል፣ የሕጋዊነት እና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ተወያይቷል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ ሪፖርቱን ለምክር ቤቱ አቅርበዋል። ዋና ኦዲተሯ በሪፖርታቸው፤ በተቋማት በጀት አጠቃቀም፣ በተሰብሳቢ ሒሳብ መጠን እንዲሁም በፕሮጀክቶች ውል መቋረጥ ላይ መሻሻሎች መታየታቸውን አንስተዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው፤ የፌዴራል ዋና ኦዲተር የኦዲት ሽፋን ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳደግ እያከናወናቸው የሚገኙት ሥራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በየዓመቱ የሚቋረጡ ፕሮጀክቶች ቁጥር እያነሰ መምጣቱን ሪፖርቱ የሚያመላክት መሆኑን ያነሱት የምክር ቤት አባላቱ፤ የኦዲት ጥራትንና ግልጽነትን ለማጠናከር በፌዴራል ዋና ኦዲተር በኩል እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችንም አድንቀዋል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው፤ የኦዲት ጥራትን ለማሻሻል በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም የተቋማትን የውስጥ ኦዲት ጥራት የሚያሻሽሉ የአቅም ግንባታ ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን ዋና ኦዲተሯ አስረድተዋል።
የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሺእመቤት ደምሴ (ዶ/ር)፤ በ2017 በጀት ዓመት ለልማት ሥራዎች ከተመደበው በጀት ውስጥ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የ99 ነጥብ 3 በመቶ የኦዲት ሽፋን ማሳካት መቻሉን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የክዋኔ ኦዲት ትግበራ በየዓመቱ እያደገ መምጣቱ የተቋሙን የኦዲት አቅም ውጤታማነት እንደሚያሳይ ገልጸዋል።
የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ አክለውም፤ በየበጀት ዓመቱ በምክር ቤቱ የሚጸድቀው የኦዲት ሽፋን ሙሉ በሙሉ እንዲካሄድና ለክዋኔ ኦዲትም በቂ ሽፋን እንዲኖር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ማድረግ ይገባቸዋል ብለዋል።
የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ፤ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ተወዳዳሪና ጠንካራ አሠራርን ለማጎልበት እያከናወናቸው የሚገኙት ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ምክትል አፈ ጉባኤዋ በየዓመቱ እየተገኙ ያሉ ለውጦችን ይበልጥ በማሳደግ እንዲሁም የታዩ ውስንነቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የቅንጅት ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አሳስበዋል።