ኢትዮጵያ በርካታ ስደተኞችን በማስተናገድ የአፍሪካውያንን የጋራ መረዳዳት እሴት በተግባር እያሳየች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በርካታ ስደተኞችን በማስተናገድ የአፍሪካውያንን የጋራ መረዳዳት እሴት በተግባር እያሳየች ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2018 (ኢዜአ):- ኢትዮጵያ በርካታ ስደተኞችን በማስተናገድ የአፍሪካውያንን የጋራ መረዳዳት እሴት በተግባር እያሳየች መሆኗን የአፍሪካ ሕብረት የመሠረተ ልማትና ኢነርጂ ኮሚሽነር ሌራቶ ማታቦጅ ገለጹ።
የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ስደተኞች በመጠለያ ጣቢያዎች ያላቸውን ሕይወት ከሀገራዊ ሥርዓቶች ጋር ማስተሳሰርን ማዕከል ያደረገ አዲስ የማካተት ፍኖተ-ካርታ ይፋ አድርጓል፡፡
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽነር ሌራቶ ማታቦጅ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ ከቀጣናው በሙሉ ለሚመጡ ስደተኞች የምታሳየውን የረጅም ጊዜ የእንግዳ ተቀባይነት ባህልና አጋርነት ሕብረቱ ትልቅ ግምት እንደሚሰጠው ገልጸዋል።
ባለፉት በርካታ አሥርት ዓመታት ኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞችን ከለላ በመስጠት ለአፍሪካውያን ኩራት የሆነውን የጋራ መረዳዳትና ኃላፊነትን በተግባር ማሳየቷን ጠቁመዋል።
አዲሱ የማካተት ፍኖተ-ካርታ በዚህ ኩሩ ታሪካዊ ቅርስ ላይ የተገነባ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም በጠንካራ አጋርነት እና ቀጣይነት ባለው የፖለቲካ ቁርጠኝነት የተደገፈ ሀገራዊ አመራር የተገኘ ትልቅ ውጤት መሆኑን አብራርተዋል።
ፍኖተ-ካርታው ስደተኞች እና አስተናጋጁ ማኅበረሰብ በጋራ ሊበለጽጉና ሊያድጉ የሚችሉባቸውን አዳዲስ ዕድሎች የሚያሳይ መሆኑንም አክለዋል።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ምክትል ዋና ጸሐፊ መሀመድ አብዲ ዋሬ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ተራማጅና አካታች የሆኑ የስደተኞች ፖሊሲዎችን በማውጣትና በማሳደግ ረገድ ለአፍሪካ በአርአያነት የምትጠቀስ ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።
አሁን ይፋ የሆነው የማካተት ፍኖተ-ካርታ የዘመናችንን እጅግ አጣዳፊና ውስብስብ የስደተኞች ፈተናዎች ለመፍታት ኢትዮጵያ ያላትን ግልጽ ራዕይና የማይናወጥ ቁርጠኝነት በአጽንኦት የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።