ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትርክት ግንባታ ያላትን የመሪነት ሚና አጠናክራ ትቀጥላለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትርክት ግንባታ ያላትን የመሪነት ሚና አጠናክራ ትቀጥላለች
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2018 (ኢዜአ):- ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትርክት ግንባታ ላይ ያላትን ቀዳሚና የመሪነት ሚና አጠናክራ እንደምትቀጥል በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
የመጀመሪያው የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ በስኬት እንዲካሄድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማት እውቅና ተሰጥቷል፡፡
በዚሁ የምስጋናና የእውቅና አሰጣጥ ስነ-ስርዓት ላይ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር)፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ፣ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ከተለያዩ ተቋማት የተወጣጡ ተወካዮችና የክብር እንግዶች ተገኝተዋል።
የመጀመሪያው የአፍሪካ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤን በፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያና በኤ.ጂ.ኤ.ቴክ ኢንተርፕራይዝ ትብብር በአዲስ አበባ ከተማ መካሄዱ ይታወቃል።
ሚያዚያ 29 እና ግንቦት 1 ቀን 2018 ዓ.ም በዓድዋ ድል መታሰቢያ በተካሄደው በዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ላይ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ተሳትፈዋል።
ተሳታፊዎቹ በአዲስ አበባና በተለያዩ የሀገሪቷ ክልሎች የተከናወኑ ታላላቅ የልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
ጉባዔው የአፍሪካን እውነተኛ ገጽታ ለዓለም ለማስተዋወቅና የዲጂታል ትርክቱን አህጉሪቱ እራሷ በባለቤትነት እንድትመራው ያለመ ሲሆን፤ እቅዱንና ዓላማውን ሙሉ በሙሉ ያሳካ ውጤታማ መድረክ ሆኖ ተጠናቋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የቦርድ ሰብሳቢ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ትርክት መገንባት ለአጠቃላይ የአፍሪካ ትርክት ግንባታ ወሳኝ መሰረት ነው።
አሁን ላይ የኢትዮጵያ ስኬቶች በስፋት መነገር መጀመራቸው አፍሪካ ቀና እንድትል እያደረጋት ከመሆኑም በላይ፤ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ለዓለም ማስተዋወቅ ተችሏል ብለዋል።
ስለ ኢትዮጵያና አፍሪካ ትክክለኛውን ታሪክና እውነታ ለዓለም ማሳወቅ ብሎም ከዚህ ቀደም የተፈጠሩ አፍራሽ ግንዛቤዎችን ለመቀየር ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህ ረገድ መገናኛ ብዙሃን የሚጫወቱትን ሚና ከመቼውም ጊዜ በላይ ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡ ፡
ጉባኤው ሊጠናከር የሚገባው በጎ ጅምር መሆኑን በመጥቀስም ለስኬቱ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ጉባኤው የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ በገነባ መልኩ እጅግ ስኬታማ ሆኖ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
በቅንጅት የተሰራው ስራ ለውጤታማነቱ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመው፤ የቱሪዝም ሚኒስቴር መሰል አህጉራዊ ፋይዳ ያላቸው ታላላቅ ጉባኤዎች በቀጣይም በተጠናከረ መልኩ እንዲካሄዱ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ሁሉ እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው፤ በጉባኤው ላይ በድምሩ ከ480 ሚሊዮን በላይ ተከታይ ያላቸው 200 የሀገር ውስጥና ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች መሳተፋቸውን ተናግረዋል፡፡
መድረኩ ኢትዮጵያ በልማት ዘርፍና ለአፍሪካ ገጽታ ግንባታ ምን ያህል ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነች እንደሆነ ማሳየት የተቻለበት መሆኑን ጠቁመው፤ የሀገሪቷን የቱሪዝም ሀብቶች ለማስተዋወቅ የረዳ ታሪካዊ ሁነት መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኤ ጂ ኤ ቴክ ኢንተርፕራይዝ ምክትል ኃላፊ ኢንጂነር አብዲ ጠና በበኩላቸው፤ ጉባኤው በአፍሪካ ያሉ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች እርስ በእርስ እንዲተዋወቁና ለጋራ ዓላማ አብረው እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን በንግግራቸው አንስተዋል።