ከጎሮ እስከ ኮዬ ፈጬ አደባባይ ያለው አዲስ የኮሪደር ልማት ስራ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ከጎሮ እስከ ኮዬ ፈጬ አደባባይ ያለው አዲስ የኮሪደር ልማት ስራ ተጀመረ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2018 (ኢዜአ):- የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከጎሮ እስከ ኮዬ ፈጬ አደባባይ ድረስ ያለውን አዲስ የኮሪደር ልማት ስራ በተቀናጀና በተደራጀ አግባብ መጀመሩን አስታወቁ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመልእክታቸው፤ ከጎሮ መታጠፊያ እስከ ኮዬ ፈጬ አደባባይ ያስጀመርነው የኮሪደር ልማት አጠቃላይ የመንገዱ ርዝመት 10 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ሲሆን፣ የመንገዱ ስፋት 70 ሜትር (ስምንት ሌን ያለው) ሆኖ ከነግሪነሪው 124 ሜትር ስፋት እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ 21 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የሳይክል መንገድ፣ 21 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና በሁለቱም በኩል 4.5 ሜትር ስፋት ያለው የእግረኛ መንገድ፣ ሰፊ የአረንጓዴ ሽፋን እንዲሁም የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ በውስጡ እንደሚኖረው አመልክተዋል።
ይህ የኮሪደር ልማት በከተማዋ ቀደም ሲል የለሙ መሰረተ ልማቶችን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያስተሳስር፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን የሚያነቃቃ እና በመንገዱ ላይ ያለውን የትራፊክ መጨናነቅ የሚፈታ መሆኑን አመልክተዋል።
መነሻውን ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ጋር ያደረገ በመሆኑም ሀገራዊ ሁነቶችን ለማስተናገድ አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥርና የአካባቢውን ስታንዳርድ በእጅጉ በሚያሳድግ ሁኔታ እንደሚሰራም ነው ያብራሩት።
በኮሪደሩ ላይ ሞሎች፣ የቢዝነስ ተቋማት እና ሌሎች ኮሚኒቲዎች እንደሚገነቡ ገልጸው ከዚህ ቀደም በመንገዱ ዙሪያ ከደረጃ በታች ይሰጡ የነበሩ አገልግሎቶችን ከፍ ባለ ደረጃ ለመስጠት በሚያስችል መልኩ በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ በትልቅ ርብርብ እንደሚሰራም ከንቲባዋ ጠቁመዋል።
ይህ ኮሪደር ከከተመዋ አልፎ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው፣ ለአካባቢው ነዋሪ ሰፊ የስራ እድል የሚፈጥር፣ አካባቢውን ወደ ትልቅ የንግድ እንቅስቃሴ የሚቀይር ነው ብለዋል።
በአካባቢው ላይ የሚኖሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ትብብራቸው እንደ ወትሮው የተጠናከረ እንዲሆንና አብረን እንድንሰራ፤ እንዲሁም በስራው ውስጥ የሚሳተፉ ኮንትራክተሮች፣ ማህበራት፣ አማካሪዎች በአጠቃላይ ባለድርሻ አካላት በትብብር በፍጥነት በጋራ እንዲሳካ ከንቲባዋ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።