ቀጥታ፡

የቀድሞው የህወሃት ቡድን ከባንዳና ከባዕዳን ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ግጭት ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ ይገኛል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2018 (ኢዜአ):- የቀድሞው የህወሃት ቡድን ከፈጸመው ግፍ ተጠያቂነት ለማምለጥ ከውስጥና ከውጭ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ጋር በመሻረክ ግጭት ለመፍጠርና በሁከት ለመኖር መወሰኑን በተግባር እያሳየ መሆኑን የስምረት ፓርቲ የምክር ቤት አባልና የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ምክትል ኃላፊ ጠዓመ ዓረዶም ገለጹ።

የስምረት ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክር ቤት አባልና የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ጠዓመ ዓረዶም በትግራይ ክልል ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በቆይታቸውም የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ተግባራዊ በሆነበት ወቅት በክልሉ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት የፈጠረ መሆኑን ገልጸው፤ በስምምነቱ መሠረት የፌዴራል መንግሥት ተቋርጠው የቆዩትን የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በአፋጣኝ ወደ ሥራ እንዲመለሱ ማድረጉን አንስተዋል።

በጦርነቱ ተሳታፊ የነበሩ ወጣቶችን በመልሶ ማቋቋም ፕሮግራም አማካኝነት ወደ ቀድሞ ኑሯቸውና ሥራቸው እንዲመለሱ ሲደረግ መቆየቱን ጠቅሰው፤ በፌዴራል መንግሥቱ የበጀት ድጋፍም ሕዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሰው የቀድሞው የሕወሃት ቡድን በህገ ወጥና እኩይ ተግባራት ላይ መሰማራቱን አንስተው፥የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመጣስ ለዳግም ጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም በስምምነቱ መሠረት የተቋቋመውን ጊዜያዊ አስተዳደር በማፍረስና ፕሬዚዳንቱን በኃይል ከሥልጣን በማውረድ፣ በህገ ወጥ ምርጫ የተሰየመውን የቀድሞውን ምክር ቤት ወደ ስራ በመመለስ አዲስ ካቢኔ ማዋቀሩን ጠቁመዋል።

ቡድኑ ከፌዴራል መንግሥት የሚመደበውን የልማት በጀት ራሱን ለዕኩይ ተግባር መልሶ ለማደራጀት እየተጠቀመበት እንደሚገኝ ነው አቶ ጣዕመ የገለጹት።

ይህንን የቡድኑን ሕገ-ወጥ አካሄድ የሚቃወሙ የትግራይ ነዋሪዎችን በማሰርና በማንገላታት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የቀድሞው የህወሃት ቡድን ከተጠያቂነት ለማምለጥ ሲል ከውስጥና ከውጭ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ጋር ጥምረት በመፍጠር፣ ክልሉን በሁከትና ብጥብጥ ውስጥ ለማቆየት መወሰኑን በተግባር እያሳየ መሆኑን አስታውቀዋል።

የቀድሞ ህወሃት በክልሉ ዳግም የጦርነት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ፓርቲያቸው ባደረገው ዳሰሳ ማረጋገጡን የገለጹት አቶ ጠዓመ፣በርካታ ወጣቶች ያለ ፍላጎታቸው በሌሊት እየታፈሱ ወደ ጦር ካምፕ እየተወሰዱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ቡድኑ ወጣቶችን ለወታደራዊ ሥልጠና ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በአስገዳጅ ሁኔታ በመላክና ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመስራት፣ ሊቀሰቅስ ያሰበውን ጦርነት ቀጣናዊ መልክ ለማስያዝ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የቀድሞው የህወሃት ቡድን ከሀገር ውስጥ ተስፋ ከቆረጡና ከውጭ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ከሚቃወሙ አካላት ጋር "ፅምዶ" የተሰኘ ጸረ ሰላም ጥምረት በመፍጠር ሀገር ለማተራመስ እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ በሕዳሴው ግድብና በቀይ ባሕር ጥያቄ ዙሪያ ያገኘችውን ዲፕሎማሲያዊ ተቀባይነት ለማጠልሸት ቡድኑ ከውስጥ ባንዳና ከውጭ ባዕድ ኃይሎች ጋር በቅንጅት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም