ኢንስቲትዩቱ የፋርማሲዩቲካል የምርምር ውጤቶችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ያለውን አጋርነት ያጠናክራል - ኢዜአ አማርኛ
ኢንስቲትዩቱ የፋርማሲዩቲካል የምርምር ውጤቶችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ያለውን አጋርነት ያጠናክራል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2018(ኢዜአ)፦ አርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት የሚያወጣቸውን አዳዲስ የፋርማሲዩቲካል የምርምር ውጤቶች ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ያለውን አጋርነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ "ምርምርና ሚዲያ ለላቀ ጤና" በሚል መሪ ሐሳብ አራተኛውን ዓመታዊ የሚዲያ ፎረም አካሂዷል፡፡
በፎረሙ ላይ ከተለያዩ የሚዲያና የኮሙኒኬሽን ተቋማት የተወጣጡ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ በኢንስቲትዩቱ የተከናወኑ የሪፎርም ስራዎችንና የምርምር ውጤቶችን በቦታው ተገኝተው ጎብኝተዋል።
የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፤ ህክምና በዓለም ላይ ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው የቀደሙ የስልጣኔ ዘርፎች አንዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የትልልቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት መስራችና የህክምና ጠበብቶች መፍለቂያ መሆኗን አመልክተዋል።
የህክምና አሰራሩ ዘመናዊ መንገድን የተከተለ ባለመሆኑ ዘርፉ እንደ እድሜው ያህል ወደፊት መጓዝ ሳይችል መቆየቱን ጠቁመው፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት ሀገር በቀል እውቀትን በዘመናዊ አግባብ መምራት በመቻሉ አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።
የህክምናውን ዘርፍ በምርምር የተደገፈ እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉም ብለዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ የመድኃኒት፣ የክትባትና የመመርመሪያ መሣሪያዎች ምርምርና ልማትን እንዲሁም የፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪውን በስፋት እየደገፈ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በዚህም ማዕቀፍ የተከናወኑ ተግባራት የሀገር ውስጥ የፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪው ከሀገር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እየሆነ እንዲመጣ ማድረጋቸውንና በአሁኑ ወቅት የክትባት መድኃኒቶች በራስ አቅም ተመርተው ለህብረተሰቡ ተደራሽ እየሆኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የኢንስቲትዩቱን የምርምር ውጤቶች ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የሚዲያ ሚና የማይተካ መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰሩ፤ በቀጣይም የሚወጡ አዳዲስ የፋርማሲዩቲካል የምርምር ውጤቶችን ለህዝብ ለማድረስ ከሚዲያ አካላት ጋር ያለው አጋርነት ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በጉብኝቱና በፎረሙ ላይ የተሳተፉት የሚዲያና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ የሀገሪቱን የህክምና ዘርፍ ለማዘመን እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት እጅግ የሚደነቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የተቋሙን የሪፎርም እና የምርምር ስራዎች በዘገባዎቻቸው ውስጥ በስፋት በማካተት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰሩ ጠቅሰዋል፡፡