በኢዜአ ዐይን…! - ኢዜአ አማርኛ
በኢዜአ ዐይን…!
በዮሐንስ ደርበው
ከተጽዕኖ ፈጣሪነትና ተደማጭነት መጎልበት እስከ የአኅጉር ድምጽ መሆን - የኢትዮጵያን ታላቅነት የገለጠው የዲፕሎማሲው ዘርፍ ስኬት
ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲያዊ ጥረቷ የፓን አፍካኒዝም ንቅናቄን በማንሳት አኅጉራዊ ተቋማት እንዲመሠረቱ ፊታውራሪ ከመሆን እስከ ለጎረቤቶቿ ሰላም ጉልኅ ሚና ተጫውታለች፤ አሁንም ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔን እያሰረጸች በርካቶች እንዲጋሯት አድርጋለች።
እንደ ሀገር ከለውጡ መንግሥት ወዲህ ከተገኙ በርካታ ትላልቅ ስኬቶች መካከል በዲፕሎማሲው ዘውግ የተመዘገበው አንዱ ነው።
የለውጡ መንግሥት የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ዋነኛ መለኪያም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ነው።
የኢትዮጵያ ሁኔታዎችን የማሰብ፣ የመፈለግና የመከወን ሂደት ንጥል (ለራስ ብቻ የሚል) ሳይሆን፤ በወንድማማችነት/እህትማማችነት ዕሳቤ በጋራ ማደግን ያነገበ እንጅ።
ይህ ሂደቷም በበርካታ ሀገራት፣ ዓለም አቀፍ እንዲሁም አኅጉር አቀፍ ተቋማት ተወድሷል። በዚህም ሐሳቦቿ ቅቡል ሲሆኑ ተመልክተናል።
ኢትዮጵያ የ#BRICS አባል መሆን መቻሏ አንዱ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ይህም ተሰሚነቷን ያረጋገጠ ማስረጃ ሲሆን፤ በኢኮኖሚ፣ በንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ተያያዥ ጉዳዮች ዘርፈ-ብዙ ጥቅም በማስገኘት የበለጸገች ኢትየጵያን ዕውን ለማድረግ የሚደረገውን ጉዞ ያፋጥናል።
ወዲህ ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባልና አፍሪካን በመወከል ምክትል ፕሬዚዳንት ሆና መመረጧም የአኅጉሪቱ ድምጽ መሆኗን ይነግረናል።
ዓለም አቀፍ ብሎም አኅጉር አቀፍ የሆኑ በርካታ ኮንፈረንሶችም በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት እንዲካሄዱ መደረጉ አንድምታው ብዙ ነው። በብቃት ማስተናገዷ ደግሞ ሌላኛው ጥንካሬዋ።
ሌላው የሀገራችንን የተጨበጠ የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ስኬት የሚገልጽልን፤ የዓለም የዓየር ንብረት ለውጥ ጉባዔን (COP32) እንድታዘጋጅ መመረጧ ነው። ይህን ትልቅ ዕድል በርካቶች ስለተመኙት አላገኙትም፤ ኢትዮጵያ ግን ዜጎቿን አስተባብራ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቁርጠኛ አመራር ሰጭነት ባከናወነችው ያላሰለሰ ትጋት አግኝታዋለች።
ግጭት ባለባቸው የቀጣናው ሀገራትም በመንግሥታቱ እንዲሁም በአፍሪካ ሕብረት ሥር ከምታበረክተው ከፍተኛ አስተዋጽዖ ባለፈ፤ በግሏ የጣረችው ብዙ ነው። ከራሷ አልፋ ለጎረቤቶቿ ዘብ መሆኗ፤ በአብሮት መኖርን እና በጋራ ማደግን በተግባር የገለጠች ሀገር ያደርጋታል።
ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ በሚለው ድሚያ ለሀገር በቀል ዕውቀቶች በሩን ክፍት ባደረገው ትጋቷም፤ በበርካታ የአኅጉሪቱ ሀገራት ዘንድ ምሥጋና አስችሯታል።
በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲዋም በተለያዩ ሀገራት በችግር ውስጥ የነበሩ ዜጎቿን ከሀገራቱ እና ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመነጋገር በተሳካ ሁኔታ ልጆቿን ወደ ዕቅፏ መልሳለች፤ በቅርቡ በሳዑዲ ዓረቢያ ለእስር ተዳርገው የነበሩ ኢትዮጵያውያን የፍርድ ሂደታቸው ተቋርጦ የምኅረት ዐዋጅ እንዲሰጣቸው መደረጉ አንድ ማሳያ ነው።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መጋቢት 22 ቀን 2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ እንዳመላከተው፤ በዓለም ዲፕሎማሲያዊ መድረኮች ተፅዕኖዋ እየጎላ እና ጥንካሬዋ እየጎለበተ የመጣው ሀገራችን አሁንም የፓን አፍሪካኒዝም ማማና የፅናት ተምሳሌት መሆኗን ለዓለም በድግሚ ያረጋገጠ የታሪክ ምዕራፍ ተገኝታለች ብሏል።
ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡት ስልታዊ የዲፕሎማሲ ድሎች የኢትዮጵያን ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ወደ ላቀ ከፍታ ማሸጋገራቸውን ጠቅሶ፤ ዛሬ ሀገራችን በውጭ ግንኙነቷ የምትታወቀው የቀጣናዊ አጀንዳዎች ምንጭና የመፍትሔ አካል በመሆን ነው ሲል ገልጿል።
በሌላ በኩል ደግሞ፤ ኢትዮጵያ አፍሪካን ጨምሮ በተለያዩ አኅጉራት በሚገኙ ሀገራት መሪዎችና ተወካዮች ዘንድ በስፋት የተመረጠችና የተጎበኘች ሀገር መሆኗን ማስታወስ ተገቢ ነው። ከጉብኝት ባለፈ ትላልቅ ስምምነቶችም የተፈራረመች መሆኗን ልብ ማለት ይገባል፤ ይህም የምታነሰውን ሐሳብ ገዥነትና የአፍሪካ መግቢያ በር መሆኗን ያሳያል።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከአጀንዳ ተቀባይነት ወደ አጀንዳ ሰጭነት በመሸጋገር ብሔራዊ ጥቅምን በሚያስጠብቅ ከፍታ እየተጓዘ መሆኑን መረዳት ይገባል።
ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ድርድር ሂደት የተጎናጸፈችው የዲፕሎማሲ ስኬት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መነቃቃት መፍጠሩንም ማጤንም ያስፈልጋል። ይህ የተሳካው ሀገሪቱ ኢትዮጵያ መንገዷም የጋራ ልማትን የሰነቀ ዕውነት በመሆኑ ነው።
በቀጣይ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለአንዲት ሀገራቸው አምባሳደር በመሆን፤ የዲፕሎማሲውን ሥራ በይበልጥ ማገዝ ይጠበቅባቸዋል። ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ካልሠሩ ማን ለሀገራቸው ሊሠራ ይችላል?
#Ethiopian_News_Agency #የኢትዮጵያ_ዜና_አገልግሎት #ዲፕሎማሲ