አዲሱ የማካተት ፍኖተ ካርታ መደመርን በተግባር የሚያሳይ እና እውነተኛ የፓን አፍሪካኒዝም መሪነትን የሚያንጸባርቅ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ የማካተት ፍኖተ ካርታ መደመርን በተግባር የሚያሳይ እና እውነተኛ የፓን አፍሪካኒዝም መሪነትን የሚያንጸባርቅ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2018 (ኢዜአ):- አዲሱ የማካተት ፍኖተ ካርታ መደመርን በተግባር የሚያሳይ እና እውነተኛ የፓን አፍሪካኒዝም መሪነትን የሚያንጸባርቅ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
የስደተኞችና ተመላሽ አገልግሎት ስደተኞች በመጠለያ ጣቢያ ያላቸው ህይወት ከብሔራዊ ስርዓቶች ጋር ማስተሳሳርን ማዕከል ያደረገ የማካተት ፍኖተ-ካርታ በይፋ አስጀምሯል።
በመርሀግብሩ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ባርሀም ሳሊህ፣ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሀሰን እንዲሁም የክልል ርእሳነ መስተዳደሮች፣ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ የቀጣናው፣ የአህጉሪቱ እና አለም አቀፍ ተቋማት ሀላፊዎች እና የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ተገኝተዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን በማስተናገድ ላይ ትገኛለች፡፡
ይህ ተግባር እንዲሁ የተመረጠ ፖሊሲ ሳይሆን የሀገሪቱ ታሪካዊ ውርስ እና የብሔራዊ ማንነቷ የማይነጠል አካል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አዲሱ የማካተት ፍኖተ ካርታ ስደተኞችን የማቀፍ የመደመር ፍልስፍናን እና እውነተኛ የፓን አፍሪካኒዝም መሪነትን ያንጸባርቃል ብለዋል።
ፍኖተ ካርታው የስደተኞችን አገልግሎት ከተበታተነ አሰራር ወደ ስልታዊ አሰላለፍ በመቀየር ዓለም አቀፍ ቁርጠኝነትን ወደ ተግባር ይለውጣልም ብለዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ባርሀም ሳሊህ በበኩላቸው፤ የማካተት ፍኖተ ካርታ በኢትዮጵያ የስደተኞች ምላሽ አሰጣጥ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለስደተኞች ማካተት ላሳዩት መሪነት፣ ራዕይ እና ቁርጠኝነት ምስጋና አቅርበዋል።
ፍኖተ ካርታው ይፋ መደረጉ ሰፊ ምክክርን፣ የጋራ ባለቤትነትን እና ለስደተኞችም ሆነ ለአስተናጋጅ ማህበረሰቦች ዘላቂ የወደፊት ሕይወትን ለመገንባት ያለውን የጋራ ቁርጠኝነት እንደሚያንጸባርቅ ተናግረዋል።
ዛሬ የፖሊሲ ማዕቀፍ ማስጀመር ብቻ ሳይሆን በክብር፣ በማካተት፣ በጽናት እና በአብሮነት ላይ የተመሰረተ ብሔራዊ ራዕይ ማረጋገጫ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ትልልቅ ፈተናዎች እየገጠሟት እንኳ ከተፈናቀሉ ወገኖች ጋር ያላትን አስደናቂ አብሮነት ማሳየቷን ገልጸው፣ ዛሬም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ትልልቅ ስደተኞችን ከሚያስተናግዱ ሀገራት አንዷ ሆና መቀጠሏን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ተራማጅ የስደተኞች ፖሊሲዎች ሀገሪቱ በዓለም አቀፉ የስደተኞች ስምምነትና በዓለም አቀፉ የስደተኞች ፎረም ላይ የገባችውን ቃል ኪዳን መሰረት ያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።