ቀጥታ፡

በምክክር ሂደቱ የታየውን ጠንካራ ትብብርና ተሳትፎ በማስቀጠል ዋናውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በስኬት መቋጨት ይገባል

ሀዋሳ፤ ሰኔ 11/2018 (ኢዜአ):- በምክክር ሂደቱ የታየውን ጠንካራ ትብብርና ተሳትፎ በማስቀጠል ዋናውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በስኬት መቋጨት እንደሚገባ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፣ ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ላለፉት አራት አመታት አካታች፣ አሳታፊና ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ መዝለቁን አስታውሰዋል፡፡

ከዚህ በመቀጠል ዋናውን የምክክር ጉባኤ ለማካሄድ የተሟላ ዝግጅት መደረጉን ገልጸው በዚሁ መሰረት ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ጀምሮ በአዲስ አበባ የሚካሄድ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የምክክር ሂደቱ ቀጥሎ ዋናው የምክክር ጉባኤ በስኬት እንዲቋጭ የዜጎች ጠንካራ ተሳትፎ፣ ድጋፍና ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በምክክር ሂደቱ እስካሁን የታየውን የስኬት ጉዞ በማስቀጠል ፍፃሜውን ለሚፈለገው ውጤት ለማብቃት የሁላችንም ትጋት ያስፈልጋል ብለዋል።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ስነሰብ ኮሌጅ የሥነጽሁፍ መምህር አምሳሌ ሀጥዬ፤ በምክክር ሂደቱ የኮሚሽኑ ብርቱ ጥረትና አጠቃላይ የህዝቡ ተሳትፎ የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል።

ምክክሩ የቆዩ ችግሮችን በመፍታት ህብረ ብሄራዊ ሀገራዊ አንድነትን ለማጽናትና ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ቁልፍ አበርክቶ የሚኖረው መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም በምክክር ሂደቱ የታየውን ጠንካራ ትብብርና ተሳትፎ በማስቀጠል ዋናውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በስኬት መቋጨት ይገባል ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የህግና ገቨርናንስ ኮሌጅ መምህር ብሩክ ደስታ፤ የምክክር ሂደቱ ለኢትዮጵያና ህዝቦቿ በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠረ መልካም እድል መሆኑን ገልጸዋል።

የእስካሁኑ ሂደት በብዙ መልኩ ዜጎች የተሳተፉበትና የአጀንዳ ማሰባሰቡም ከሁሉም አቅጣጫዎች አካታች በሆነ መልኩ የተካሄደ መሆኑን ተገንዝበናል ብለዋል።

በታሪክ አጋጣሚ የተገኘውን ይህንን መልካም እድል በአግባቡ በመጠቀም ለሀገራዊ ችግሮች በምክክር መፈትሄ አበጅቶ መቋጨት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም በምክክር ሂደቱ የታየውን የዜጎች ጠንካራ ትብብርና ተሳትፎ በማስቀጠል ዋናውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በስኬት ማጠናቀቅ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

በዩኒቨርስቲው የማህበራዊ ሳይንስና ስነሰብ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ እንዳልካቸው ጀንበሬ (ዶ/ር)፤ በምክክሩ የእስካሁኑ ሂደት የሁሉም ትብብርና ተሳትፎ በጉልህ የታየበት መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም በመጨረሻ የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ መትጋት ለስኬታማነቱም መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

የዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ጀምሮ በአዲስ አበባ የሚካሄድ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መግለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም