አሜሪካ በኢትዮጵያ ሰላምን በሚያደፈርሱ ጽንፈኛ የሕወሃት አመራሮች ላይ የቪዛ እገዳ ጣለች - ኢዜአ አማርኛ
አሜሪካ በኢትዮጵያ ሰላምን በሚያደፈርሱ ጽንፈኛ የሕወሃት አመራሮች ላይ የቪዛ እገዳ ጣለች
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2018 (ኢዜአ):- አሜሪካ በኢትዮጵያ ሰላምን ለማደፍረስ እና ግጭት ለመቀስቀስ እየተንቀሳቀሱ በሚገኙ የቀድሞ የህወሓት ጽንፈኛ አመራሮች እና በቅርብ የቤተሰብ አባሎቻቸው ላይ የቪዛ እገዳ መጣሏን አስታወቀች።
የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ማዕቀቡ የተጣለው በኢሚግሬሽንና ዜግነት ሕግ አንቀጽ 212(a)(3)(C) በተሰጣቸው ሥልጣን መሠረት መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ የቪዛ እገዳ በትግራይ ክልል ያለውን ቀውስ ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶችን በሚያደናቅፉ፣ ሰላምን በሚያናጉ የሕወሃት ጽንፈኛ አባላትና የቅርብ የቤተሰብ አባሎቻቸው ላይ ያነጣጠረ ነው።
አሜሪካ በሰላምና በክብር መኖር ከሚፈልገው የትግራይ ክልል ሕዝብን ጨምሮ ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን እንደምትቆም አስታውቃለች።
በቀጣናው ሰላምና መረጋጋትን አደጋ ላይ የሚጥሉ የሕወሃት ባለሥልጣናትንና ሌሎች ግለሰቦችን ድርጊት ለማጋለጥ እንዲሁም ተጠያቂነትን ለማስፈን ዋሽንግተን ያሏትን ዲፕሎማሲያዊ አማራጮች በሙሉ መጠቀሟን እንደምትገፋበትም ገልጻለች።