ቀጥታ፡

ስትራቴጂካዊ አጋርነት እና ጂኦ-ፖለቲካዊ ስኬት-የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ጉዞ

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረክ ላይ ያላት ስም፣ዝና እና ተፅዕኖ በአጋጣሚ የተገኘ ሳይሆን፣ዘመናትን በተሻገረ ነፃነት፣በጽኑ ሉዓላዊነትና በብሔራዊ ክብር ላይ የተገነባ የረጅም ዘመን ታሪክ ውጤት ነው።

በታሪኳ ያጋጠሟትን የቅኝ ግዛት ወረራ ሙከራዎች በጀግንነትና በዲፕሎማሲያዊ ጥበብ በመመከት፣የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የነፃነት፣የኩራትና የሉዓላዊነት ተምሳሌት ሆና መውጣት ችላለች።

ይህ በአድዋ ድል የተመሰከረው ታሪካዊ እውነታ፣ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ድምፅ ለሌላቸው ወገኖቿ በነፃነት እንድትሟገትና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዋና ተዋናይ እንድትሆን የሞራል ልዕልናን አጎናጽፏታል።

የዓለም መንግሥታት ማኅበርና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (UN) ግንባር ቀደም መሥራች በመሆን ዓለም አቀፍ ተቋማት ምስረታ ላይ ታሪክ የማይረሳው አሻራ አላት።በአህጉራዊ ድርጅቱ ምስረታና ማዕከልነት ላይ ያላት ተሳርትፎም የዚሁ ማሳያ ነው።

ዛሬ ላይ በቀጣናዊ ሰላም ማስከበር፣ በናይል ተፋሰስ የፍትሐዊ ውሃ አጠቃቀም ድርድሮችና እንደ ብሪክስ (BRICS) ባሉ አዳዲስ ዓለም አቀፍ የጂኦ-ፖለቲካ ጥምረቶች ውስጥ ስኬታማ ሆና መቀጠሏን ያመላክታል።

የዓለም መሪዎች ከስትራቴጂካዊ አጋርነት እስከ ቀጣናዊ ትብብር አላማ ያደረጉ ጉብኝቶችን በአፍሪካ መዲና ኢትዮጵያ አድርገዋል።ጉብኝቶቹ የኢትዮጵያን ጂኦ ፖለቲካዊ ጠቀሜታ የሚያሳዩ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ከፍታ ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ ባደረጓቸው ጥረቶችም የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ፣ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የቱርኪዬ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን፣ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ፣የማሌዥያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሰሪ አንዋር ኢብራሒም ፣የሲንጋፖር ጠቅላይ ሚኒስትር ላውረንስ ዎንግ የእስራኤል ፕሬዝዳንት ኢሳቅ ሄርዞግ፣ የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ዋድፑል እና ሌሎችም ታላላቅ መሪዎችና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች የአዲስ አበባ ቤተኛ አድርጓቸዋል።

መሪዎቹ ኢትዮጵያን የሰላም፣የብልጽግና እና የኢኖቬሽን አጋር ናት ሲሉም ይገልጿታል።

በኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ የተደረጉ የከፍተኛ ደረጃ ጉብኝቶችም ጉብኝት ብቻ ሆነው ያለፉ አይደሉም። ኢትዮጵያ በቀጣናው እና ዓለም የዲፕሎማሲ መድረክ ያላትን ተሰሚነት የሚያሳዩ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በኦፊሴላዊ ጉብኝታቸውም ሆነ ወደ ኢትዮጵያ ከሚመጡ የሃገራት መሪዎችና ዲፕሎማቶች ጋር ያደረጓቸው ውይይቶች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ላይ ያተኮሩ የጋራ ተጠቃሚነትንም መነሻ ያደረጉ ናቸው።

በአጠቃላይ፣የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ በችግሮችና በትግሎች ውስጥ አልፎ የሀገርን ሕልውና ያቆየ፣ቀጣናዊ ግንኙነትን የፈጠረና አህጉራዊ ትስስርን ያረጋገጠ ታላቅ ጉዞ ነው።

በለውጡ ዓመታት በተጠናከረ መልኩ በቀጠለውና ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅምና ዓለም አቀፍ ተደራሽነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገሩም ናቸው።

ሀገሪቱ ያጋጠሟትን ዘመኑ የፈጠራቸውን ውስብስብ የውጭ ጫናዎች በብልሃት በመመከት፣ እንደ ብሪክስ (BRICS) ያሉ ዓለም አቀፍ ጥምረቶች ሙሉ አባል መሆን መቻሏና የሕዳሴው ግድብ የውሃ ዲፕሎማሲን በድል ማጠናቀቋ የለውጥ ዓመታቱ ደማቅ አሻራዎች ናቸው።

እነዚህ ስኬቶች ኢትዮጵያ በተለዋዋጭ የዓለም ፖለቲካ ውስጥ ያላትን ስትራቴጂካዊ ተፈላጊነት ከማሳደጋቸውም በላይ፣የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና ቀጣናዊ ተሰሚነት በአስተማማኝ መሠረት ላይ አስቀምጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም