ቀጥታ፡

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ለቤቶች ልማት የአገር ውስጥ የፋይናንስ አቅምን በውጤታማነት ለመጠቀም እየሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2018 (ኢዜአ):- የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ለቤቶች ልማት ፕሮጀክቶች የአገር ውስጥ የፋይናንስ አቅምን በውጤታማነት ለመጠቀም እየሰራ እንደሚገኝ የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል (ዶ/ር) ገለጹ።

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን እና የኦሮሚያ ባንክ የስትራቴጂካዊ አጋርነት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል (ዶ/ር) እና የኦሮሚያ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተፈሪ መኮንን ናቸው።


 

ኮርፖሬሽኑ ለሚያከናውናቸው የቤት ልማትና ተያያዥ ሥራዎች አስተማማኝ የፋይናንስ ስትራቴጂካዊ አጋርነትን በማረጋገጥ ረገድ ስምምነቱ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ተመላክቷል።

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል (ዶ/ር)፤ ኮርፖሬሽኑ ለሚያከናውነው ሰፊ የቤት ልማት ፕሮግራም የአገር ውስጥ የፋይናንስ አቅምን በውጤታማነት ለመጠቀም በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

የኦሮሚያ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተፈሪ መኮንን በበኩላቸው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስሙ በለውጥና በስኬት ከሚነሳው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ጋር በትብብር መሥራት ለአገር ኢኮኖሚ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

ሁለቱ ወገኖች ለስምምነቱ ተፈጻሚነት ያላቸውን ከፍተኛ ቁርጠኝነት መግለጻቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም