ቀጥታ፡

ስደተኞችን የማካተት ፍኖተ ካርታ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ የልማት ዕቅዶች ጋር የተጣጣመ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2018(ኢዜአ)፦ ስደተኞችን የማካተት ፍኖተ ካርታ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ የልማት ዕቅዶች እና ስትራቴጂዎች ጋር ሙሉ በሙሉ የተጣጣመ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ።

ሚኒስትሩ የልማት አጋሮችና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ስደተኞችን የሚያስተናግዱ አካባቢዎችን እንደ ሁለተኛ አማራጭ ሳይሆን፣ እንደ ሀገራዊ ቅድሚያ የሚሰጣቸው የልማት ሥራዎች አድርገው በትኩረት ሊመለከቷቸው እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ስደተኞች በመጠለያ ጣቢያዎች ያላቸውን ሕይወት ከሀገሪቱ ብሔራዊ ሥርዓቶች ጋር ማስተሳሰርን ማዕከል ያደረገውን የማካተት ፍኖተ ካርታ በይፋ አስጀምሯል።


 

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ባርሀም ሳሊህ፣ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሐሰን፣ የክልል ርእሳነ መስተዳድሮች፣ የዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ተቋማት መሪዎች እንዲሁም የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ተገኝተዋል።

ይህ ፍኖተ ካርታ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ከፌደራልና ክልል መንግሥታት፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ እንዲሁም ከሀገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ያዘጋጀው መሆኑ ተገልጿል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ እምብርት ላይ የምትገኝ ሀገር መሆኗን ጠቅሰዋል።

ሚኒስትሩ በቀጣናው ያለው ግጭትና የአየር ንብረት መዛባት ያስከተለው መፈናቀል በስደተኛ አስተናጋጅ ሀገር ላይ ተጨማሪ ጫና መፍጠሩንና አዲሱ ፍኖተ ካርታ ይህንን እርስ በርስ የተሳሰረ ችግር ለመፍታት የታለመ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጥበቃ እያደረገች ትገኛለችም ብለዋል።

ይህን የምታደርገው ሰብአዊ ኃላፊነት በመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ለቀጣናዊ ሰላም፣ ህልውና እና መረጋጋት ስልታዊ አስተዋፅዖ ስላለው ጭምር መሆኑን ጠቅሰዋል።

የማካተት ፍኖተ ካርታው የኢትዮጵያን ስደተኞችን የመንከባከብ የረጅም ጊዜ ጉዞ ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ፍኖተ ካርታው ከሀገራዊ ግቦች ጋር በቀጥታ ይተሳሰራል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ከ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ እና ከአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ ጋር፣ በምግብ ራስን ለመቻል ከሚደረገው ጥረትና ከታዳሽ ኃይል መስፋፋት ጋር እንዲሁም ከከተማ ትራንስፎርሜሽን፣ ከዲጂታል ኢትዮጵያ፣ ከዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም እና በሰው ሀብት ልማት ላይ ከሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች ጋር ይገናኛል ብለዋል።

የስደተኞች ማካተት በሰብአዊ እርዳታ ብቻ ሊደገፍ እንደማይችልና ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት የልማት ፋይናንስ እና የአየር ንብረት ፋይናንስ ማግኘት፣ የግል ዘርፍ ኢንቨስትመንትን ማበረታታት፣ እውነተኛ ዓለም አቀፍ የልማት ኃላፊነትን በጋራ መጋራት ወሳኝ መሆናቸውን አሳስበዋል፡፡

ኢትዮጵያ እያከናወነችው ያለው ተግባር ለቀጣናው እንዲሁም ለዓለም መረጋጋት፣ ጥንካሬ እና ብልጽግና የተደረገ ትልቅ ኢንቨስትመንት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ሀገሪቱ ከጎረቤት ሀገራት፣ ከቀጣናዊ ድርጅቶች፣ ከልማት ተቋማት እና ከአለም አቀፍ አጋሮች ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኗን በድጋሚ አረጋግጠዋል።

የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሀሰን በበኩላቸው፤ የዛሬው እለት በኢትዮጵያ የስደተኞች ማካተት ጉዞ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም የገባናቸውን ቃል ወደ ተግባርና ወደ ሚለኩ ውጤቶች ለመቀየር ያለንን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያንጸባርቅ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም