መገናኛ ብዙሃን የሀገርን ዘላቂ ሰላም በማስቀደም ለህብረ ብሔራዊ አንድነት መጠናከር የላቀ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙሃን የሀገርን ዘላቂ ሰላም በማስቀደም ለህብረ ብሔራዊ አንድነት መጠናከር የላቀ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል
ሀዋሳ፤ ሰኔ 11/2018(ኢዜአ)፦ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅምና ዘላቂ ሰላም በማስቀደም ለጋራ ትርክት ግንባታና ለህብረ ብሔራዊ አንድነት መጠናከር መገናኛ ብዙሃን የላቀ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) ገለጹ።
የሀገርና የህዝብን ሰላም በዘላቂነት አጠናክሮ ለማስቀጠልም ትክክለኛና ተጨባጭ መረጃዎችን በሃላፊነት መንፈስ ማቅረብ እንዳለባቸውም አስታውቀዋል።
የሰላም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ጋር በመተባበር "የሚዲያ ተቋማት ሚና ለሰላም ግንባታ" በሚል መሪ ሃሳብ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር በሐዋሳ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) ፤ ሀገር ጸንታ መቆየት የምትችለው ሰላም በዘላቂነት ሲረጋገጥ መሆኑን ገልጸው፣ መገናኛ ብዙሃን በዘገባዎቻቸው የህዝብን ሰላም የሚያጸኑ ሥራዎችን መስራት አለባቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን በሰላም፣ በመረዳዳት፣ በፍቅርና በአብሮነት ለዘመናት አብረው እንዲቆዩ ያስቻሉ እሴቶችን አጠናክረው በማስቀጠል እርስ በርስ መቀራረብ እና መቻቻል እንዲጎለበት ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የሀገርን ብሔራዊ ጥቅምና ዘላቂ ሰላም በማስቀደም ለጋራ ትርክት ግንባታና ለህብረ ብሔራዊ አንድነት መጠናከር በትጋት እንዲሰሩም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ግጭቶችን በመፍጠር የሀገርን ሰላምና ልማትን ለማደናቀፍ እያደረጉት ያለውን ዘመቻ ለመመከት መገናኛ ብዙሀን በሀላፊነት መንፈስ እንዲሰሩም አሳስበዋል።
በሥራዎቻቸው ሰላምን ዋነኛ አጀንዳ ከማድረግ ባለፈ በብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ ዜጎች የጠራ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
የዲጂታል ሚዲያ መስፋፋትን ተከትሎ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዘ ሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር መበራከቱንና በሀገርና በህዝብ ሰላም ላይ የራሱን ተጽዕኖ እያሳደረ መምጣቱን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛው ተስፋዬ ናቸው።
መገናኛ ብዙሀን ይህን መርምሮ በማጥራትና ትክክለኛ መረጃን በማቅረብ ህዝብ እውነታውን እንዲያውቅ ማድረግና ሊፈጠር የሚችለውን ችግር ቀድሞ መከላከል እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ህዝቡ ለሰላሙ ዘብ እንዲቆም የውይይት መድረክ መሆን እንዳለባቸው ገልጸው፣ ግጭት ሲከሰትም ሰላምና መረጋጋት ወደነበረበት እንዲመለስ የሚያደርጉ ስራዎችን መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዘላለም ገነሞ እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የተዛቡ መረጃዎች በሀገርና በህዝብ ሰላም ተዕዕኖ እያሳደሩ ነው፡፡
ድርጅታቸውም በተለያዩ የብሔረሰብ ቋንቋዎች የተጣራና ትክክለኛ መረጃ ለህዝብ ከማድረስ ባለፈ በዘላቂ ሰላም አስፈላጊነት ላይ የማህበረሰቡን ግንዛቤ የሚያሳድጉ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች ማህበርን ወክለው በመድረኩ ከተሳተፉት ውስጥ አቶ እስማኤል ጠሀ እንዳሉት፤ በሀገሪቱ 40 የማህበረሰብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ፈቃድ አውጥተው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።
ጣቢያዎቹ ስርጭታቸው በሚተላለፍበት አካባቢ ከ25 በሚበልጡ ቋንቋዎች ሰላምና እንድነትን የሚያጸኑ ሥራዎችን ለህዝቡ እያደረሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በመድረኩ ከሲዳማ፣ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ከደቡብ ኢትዮጵያና ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች የሚዲያ አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።