ቀጥታ፡

በሲዳማ ክልል ሸበዲኖ ወረዳ ከ312 ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት የሚያስችል የፀሀይ ኃይል ማመንጫ ሊገነባ ነው

ሀዋሳ፤ ሰኔ 11/2018(ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል ሸበዲኖ ወረዳ ከ312 ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት የሚያስችል የፀሀይ ኃይል ማመንጫ ሊገነባ ነው። 

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሡልጣን ወሊ (ዶ/ር) የግንባታ ፕሮጀክቱን ያስጀመሩ ሲሆን ግንባታው ሲጠናቀቅ ለመስኖ ልማት ስራ ትልቅ አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት የመውጣትና የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ጥረት በተቀናጀ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ለዚህም የመስኖ ልማትን ይበልጥ የማስፋፋትና ያልታረሱ መሬቶችን ማልማት አስፈላጊ መሆኑን አንስተው ለልማቱ ስኬት የሃይል ልማትን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

በግብርና ልማቱ በነዳጅ ኃይል የሚሰሩ የመስኖ ፕሮጀክቶች መስተጓጎል እንዳይገጥማቸው የጸሃይና ሌሎች የሃይል አማራጮችን መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

በዚሁ መሰረትም በሲዳማ ክልል ሸበዲኖ ወረዳ በአሳራዶ ሜሮ ቀበሌ የሚገነባው የፀሀይ ኃይል ማመንጫ ከ312 ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

የፕሮጀክቱ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከ312 ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ከማልማት በተጨማሪ ከ800 በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው አርሶ አደሮች ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚሰጥ ይሆናል ብለዋል።

የሲዳማ ክልል ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ከበደ ጋኖሌ፤ የፕሮጀክቱ ግንባታ ከኤሌክትሪክ አገልግሎት መስመር ለራቁ ገጠራማ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሁም ለመስኖ ልማት የሃይል ምንጭ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።


 

አካባቢው የአቮካዶና መሰል የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የቡና ልማት ሰፊ አማራጭ ያለበት በመሆኑ የፕሮጀክቱ ግንባታ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑንም አንስተዋል።

የከርሰና ገጸ ምድር የውሃ አማራጭን በመጠቀም የእርሻ ስራን የማጠናከር ስራ በስፋት መቀጠሉን ጠቅሰው ባለፉት አምስት ዓመታት ከ60 በላይ የመስኖ ፕሮጀክቶች መገንባታቸውንም አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም