ቀጥታ፡

በምስራቅ ወለጋ ዞን ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በኢንቨስትመንት ዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን እየሰራን ነው-ባለሀብቶች 

ነቀምቴ፤ ሰኔ 11/2018(ኢዜአ)፦ በምስራቅ ወለጋ ዞን ለኢንቨስትመንት ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ውጤታማ ለመሆን እየሰሩ መሆናቸውን በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሀብቶች ገለጹ።

በዞኑ ሊሙ ወረዳ በግብርናው ዘርፍ በበቆሎ ምርት ላይ የተሰማሩት ባለሀብት አቶ አበራ ጎሹ እንደገለጹት፤ በአካባቢው ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የግብርና ምርትና ምርታማነትን እያሳደጉ ይገኛሉ።

በዚህም ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውን ተናግረው በ8 ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል በ100 ሄክታር መሬት ላይ በቆሎ እያመረቱ መሆኑን ገልጸዋል።

የግብርና ሥራውን በማዘመን ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ መሆኑንና ይህም ለአካባቢው አርሶ አደሮች ጥሩ አርዓያ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል።

በእርሻ ስራውም ለ9 ሰዎች ቋሚ፣ እንዲሁም በምርት ወቅት ከ50 እስከ 60 ለሚደርሱ ነዋሪዎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን አስረድተዋል።

ሌላኛው ባለሀብት አቶ ረጋሳ ኤጄታ በበኩላቸው፣ በሲቡ ስሬ ወረዳ ለሊሳ ቀበሌ በግብርና ሥራ ላይ መሰማራታቸውን ገልጸዋል።

መንግስት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ዜጎች በተሰማሩበት ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆኑ እያደረገ ያለውን ድጋፍና ምቹ ሁኔታ በመጠቀም እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ባለሀብቱ በቆሎ፣ ሩዝ፣ ኑግ እና አኩሪ አተር የተሻለ ምርት የሚገኝባቸው ሰብሎች መሆናቸውን ገልጸው በምርት ወቅት  ከ100 እስከ 150 ለሚደርሱ የአካባቢው ነዋሪዎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

የምስራቅ ወለጋ ዞን ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ ተስፋ፤ በዞኑ ሰፊ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ መኖሩን ገልጸው፤ ባለሀብቶች በተለይም በማኑፋክቸሪንግ፣ በማዕድን እና በግብርና ዘርፎች ላይ በስፋት መሰማራታቸውን ተናግረዋል።

በዞኑ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች 1 ሺህ 392 ባለሀብቶች በሥራ ላይ መሆናቸውን ገልጸው እነዚህ ባለሀብቶች በ2 ቢሊዮን ብር ካፒታል እየተንቀሳቀሱ ነው ብለዋል።

በዞኑ በተመቻቸው የኢንቨስትመንት ዕድል 66 ሺህ ሄክታር መሬት ለባለሀብቶች የተሰጠ ሲሆን እስካሁን ከ26 ሺህ በላይ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ተናግረዋል።

ዞኑ በተለይ ለግብርና ሥራዎች ተመራጭ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው፤ በቆሎ፣ የቅባት እህሎች፣ የጥራጥሬ ሰብሎች፣ ቡና እና ሌሎች የአገዳ እህሎች በስፋት የሚመረቱበት አካባቢ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሰረተ ልማት አቅርቦት ረገድ ያሉ ጥያቄዎችንም ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም