የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሀገሪቷን ዓለም አቀፍ ተሰሚነትና ስትራቴጂካዊ ተጠቃሚነት ወደ ላቀ ከፍታ ማደጉን የሚያረጋግጥ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሀገሪቷን ዓለም አቀፍ ተሰሚነትና ስትራቴጂካዊ ተጠቃሚነት ወደ ላቀ ከፍታ ማደጉን የሚያረጋግጥ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷና በዓለም አቀፍ መድረኮች የምታሳየው ንቁ ተሳትፎ፣ የሀገሪቷን ዓለም አቀፍ ተሰሚነትና ስትራቴጂካዊ ተጠቃሚነት ወደ ላቀ ከፍታ ማደጉን የሚያረጋግጥ ነው ሲሉ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ምሁራን ገለጹ።
ምሁራኑ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በ2018 በጀት ዓመት ባደረገችው እንቅስቃሴ በውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ መስክ ያስመዘገበቻቸውን ስኬቶች ዘላቂ ለማድረግ የበለጠ መሥራት ይገባታል።
በኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ ባይሳ ተስፋዬ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አዲስ አበባ ከተማ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማትን በሚመጥን መልኩ መቀየሯ ለዲፕሎማሲው ግንኙነት ትልቅ አቅም ፈጥሯል፡፡
በአዲስ አበባ የተከናወኑት የከተማ ልማት፣ ማስዋብ እና የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከተማዋን የዓለም የዲፕሎማሲ መስህብ ማድረጉን አመልክተው፤ ይህም የከተማዋን ተወዳዳሪነት ከማሳደጉም በላይ ዓለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን እምነት በማሳደግ ሌሎች ድርጅቶችም ወደ ሀገሪቷ ለመምጣት እንዲወስኑ መንገድ መክፈቱንም ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች በመምጣት የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን የማደስና የማጠናከር ተግባር ማከናወናቸውን ጠቅሰው፤ የዚህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያን ተሰሚነትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት እየጨመረ መምጣቱን እንደሚያረጋግጥ ገልጸዋል።
በተጨማሪም የአገራት መሪዎች ጉብኝት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማጠናከርና ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላቸው የሚያሳይ መሆኑን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የጣሊያን-አፍሪካ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስርዓተ-ምግብ ጉባኤዎችን በስኬት ማስተናገዷን አስታውሰው፤ ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ኮንፈረንሶችን በብቃትና በጥራት በማስተናገድ መልካም ስም ማግኘቷ የዓለምን ትኩረት በከፍተኛ ሁኔታ መሳብ እንዳስቻላት ነው የተናገሩት።
እነዚህ ስኬቶች የመጡት በሀገር ደረጃ በተከናወኑ ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎችና ውጤታማ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የትብብር መድረኮች ያላት ተሳትፎ በየጊዜው እያደገ መምጣቱን ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅት የሁለትዮሽና የብዝሃ ግንኙነትን በማጠናከርና አዳዲስ ወዳጆችን በማፍራት በኩል በሳል የዲፕሎማሲ ግንኙነት መደረጉን ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት የብሪክስ (BRICS) ሙሉ አባል ለመሆን መቻሏን በአብነት ገልጸዋል።
በተጨማሪም የዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) አባል ለመሆን እየተከናወነ ያለው ሥራ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ውስጣዊ ፍላጎቷን እንድታስከብርና ድርሻዋን እንድትወጣ ያግዛታልም ብለዋል።
በአገር ውስጥ የሚሰሩ የአቅም ግንባታ ሥራዎችም ለዓለም አቀፍ ተሰሚነቱ መነሻ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ ለዚህ ማረጋገጫ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ስለሆነም የኢትዮጵያን ቀጣናዊ የመሪነት ሚና ለማስቀጠል፣ የውስጥ አቅምን መገንባት፣ በአንድነት መቆም እና ሁለንተናዊ ልማትን ለማፋጠን መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡
በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል የውጭ ግንኙነት ፖሊሲና ዲፕሎማሲ መምህር አበራ ሄቢሶ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ከለውጡ ወዲህ በፍጥነት እያደገ ያለ የዲፕሎማሲ ሥራ ማከናወን መቻሏን ገልጸዋል።
በተለይም በተያዘው ዓመት የጣሊያን፣ ሕንድ፣ ቱርክና ፈረንሳይን ጨምሮ የተለያዩ የዓለም ሀገራት መሪዎች በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት ማድረጋቸው የሀገሪቷን ተሰሚነት ከፍ ያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ይህም ሀገራቱ ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ መሥራት የጋራ ተጠቃሚነትን እንደሚያረጋግጥ በመገንዘባቸው የመጣ ስኬት መሆኑን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በመርህ ላይ የተመሰረተ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ እንደምትከተል ጠቅሰው፤ የብሪክስ አባልነቷም በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ያላትን የመደራደር አቅም በእጅጉ እንደሚያጎለብተው አስገንዝበዋል።
በአዲስ አበባ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች የከተማዋን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት የሚመጥኑና የሀገሪቱን ገጽታ ከፍ ያደረጉ መሆናቸውን ያብራሩት መምህር አበራ፤ ኅብረተሰቡ ወደ ሀገር ውስጥ የሚመጡ እንግዶችን በኢትዮጵያዊነት የቆየ የእንግዳ ተቀባይነት ባህል ማስተናገዱን አጠናክሮ ሊቀጥልበት እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።