በስርዓተ ምግብ አለመስተካከል የሚከሰቱ ችግሮችን ለመከላከል ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በስርዓተ ምግብ አለመስተካከል የሚከሰቱ ችግሮችን ለመከላከል ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ትኩረት ተደርጓል
ሆሳዕና ፤ ሰኔ 11/2018(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በስርዓተ ምግብ አለመስተካከል የሚከሰቱ ችግሮችን ለመከላከል ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ትኩረት መደረጉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለፁ።
በክልሉ ስርዓት ምግብ ሽግግርና የቀዳማዊ ልጅነት ልማት ፍኖተ ካርታ ማስጀመሪያ የውይይት መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሄዷል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በክልሉ በስርዓተ ምግብ አለመስተካከል የሚከሰቱ ችግሮችን ለመከላከል ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ትኩረት ተደርጓል።
በክልሉ በግብርናው ዘርፍ ያሉትን አቅሞች አሟጦ በመጠቀም ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
በተለይም የሌማት ትሩፋት ትግበራው የተመጣጠነ ምግብ ለማግኘት አስቻይ ሁኔታን እየፈጠረ ስለመምጣቱም ጠቁመዋል።
በስርዓተ ምግብ እጥረት የሚከሰቱ ችግሮችን በመከላከል ጤናማና አምራች ዜጋን ለመፍጠር እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማጠናከር ክልሉ ያሉትን አማራጮች ሁሉ ተግባራዊ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ተወካይ አቶ ደበሌ ደበላ፤ የኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት ሽግግር ፍኖተ ካርታ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከዘላቂ የልማት ግቦች ጋር በማስተሳሰር ሲተገበር እንደቆየ አስታውሰዋል።
በኢትዮጵያ በቀዳማይ ልጅነት ወቅት የሚከሰቱ የስርዓተ ምግብ ችግሮችን ለመፍታት ፈጠራን፣ የሜካናይዜሽን ግብርናን፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂንና የግሉን ዘርፍ ማበረታታት እንደሚገባም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ቀዳማዊ ልጅነት ፕሮግራም ከፍተኛ አማካሪ ሰለሞን ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደገለፁት የህፃናት አዕምሮ ወቅቱን በሚመጥን መልኩ ተገንብቶ ማደግ አለበት።
ተቻችሎና ተከባብሮ የሚኖር፣ መፍትሄን ከነፍጥ የሚያስቀድም ዜጋን ለመፍጠር በቀዳማይ ልጅነት ላይ መስራት እንደሚገባ በሀገር አቀር ደረጃ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተተገበረ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በዚህም የትውልድ ግንባታውን ለዘላቂ እድገት ለመጠቀም የሚያስችሉ ተግባራት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች መተግበር መጀመሩን ገልጸው ይህም ክልል የዚሁ ተግባር ተጠቃሚ ለመሆን ያሳየው ቁርጠኝነት የሚበረታታ ስለመሆኑም አስረድተዋል።
"የቀዳማዊ ልጅነት ፕሮግራም ትግበራ ህፃናትን በሁሉም ዘርፍ የበቁና በራሳቸው የሚተማመኑ ዜጎች እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዘቢባ መሀመድናስር ናቸው።
ለዚህም ስኬት በክልሉ ከተሞች ለህፃናት ምቹ የመጫወቻና የሚዝናኑበት ስፍራን ከመለየት አንስቶ እየተሰራ ያለው ስራ እንደሚጠናከር ገልጸዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የፌዴራል፣ የክልል፣ የዞንና የልዩ ወረዳ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።