ቀጥታ፡

በዞኑ የገቢ ምንጭን ለማስፋት እና ግንዛቤን ለማሳደግ በተሰራው ስራ ከዕቅድ በላይ ገቢ መሰብሰብ ተችሏል

ጅማ ፤ ሰኔ 11/2018(ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን የገቢ ምንጭን ለማስፋት እና ግንዛቤን ለማሳደግ በተሰራው ስራ በዘንድሮው ዓመት ከዕቅድ በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉ ተመላከተ፡፡

በዞኑ ባለፉት አስራ አንድ ወራት 10 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን የዞኑ ገቢዎች ፅህፈት ቤት አስታውቋል። 

የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ካሳሁን ታደለ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የገቢ ምንጭን ለማስፋት እና ግንዛቤን ለማሳደግ በተሰራው ስራ በዘንድሮው ዓመት ከዕቅድ በላይ ማከናወን ተችሏል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ 9 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 10 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በመሰብሰብ 116 በመቶ ከዕቅድ በላይ ማከናወን ተችሏል ብለዋል።

ኃላፊው አክለውም ይህ ገቢ ከመደበኛ፣ መደበኛ ካልሆኑ እና ከማዘጋጃ ቤት አገልግሎት የተሰበሰበ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በዚህ ዓመት መንግስት የገቢ ምንጭን ለማስፋት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ለማዕከላዊ ገበያ ከሚቀርብ ቡና የተሻለ ገቢ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

በዞኑ ከ27 ሺህ በላይ የንግድ ተቋማት መኖራቸውን ጠቅሰው የመንግስት እና የግል ተቋማትን ጨምሮ ከልዩ ልዩ የገቢ ምንጮች በጥንቃቄ መሰብሰቡ እና የግብር ከፋዩ ግንዛቤ እያደገ መምጣቱ ለተገኘው ውጤት ዋና ምክንያት ነው ብለዋል።

የገቢ አሰባሰብ ሂደት መዘመን እና በቴክኖሎጂ መታገዝ ለቁጥጥር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የተናገሩት አቶ ካሳሁን ይህም አሰራሩን ቀላል አድርጎታል ብለዋል።

በቀጣይም የማህበረሰቡን ግንዛቤ ይበልጥ በማስፋት የበለጠ ውጤታማ ለመሆን እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።


 

የጅማ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ በፍቃዱ ታሪኩ፣ የግብር አከፋፈል ሂደቱ ከዚህ ቀደም ከነበረው ሁኔታ እጅግ የተሻሻለ መሆኑን ጠቅሰው በተለይም በቴክኖሎጂ የታገዘ መሆኑ ጊዜዬን ቆጥቦልኛል ብለዋል።

የተሽከርካሪ ግብር ክፍያን በየጊዜው ገቢ እንደሚያደርጉ የሚናገሩት አቶ ሙሉቀን ጎሹ እና ጌታሁን ግርማ መንግስት ያስቀመጠው የግብር አከፋፈል ሂደት ምቹ እና ዘመናዊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከዚህ ቀደም የነበሩ ችግሮች ተቀርፈው ግልፅነት በተሞላበት መልኩ የተሻለ አገልግሎት እያገኘን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም