ቀጥታ፡

የአፍሪካ የዓለም ዋንጫ የተሳትፎ ታሪክ፤ ከአብዱልራህማን ፋውዚ ታሪካዊ ጎሎች እስከ ሞሮኮ አስደናቂ ገድል

በሙሴ መለሰ

የአፍሪካ የዓለም ዋንጫ ጉዞ የጽናት፣ የድንቅ ድሎችና የታሪክ ለውጥ ተምሳሌት ነው። አህጉሪቱ ጥቂት ዕድሎችን ለማግኘት ከነበረባት ፈታኝ ጅማሮ ተነስታ፣ ዛሬ በዓለም እግር ኳስ ውስጥ  ተፅእኖ ፈጣሪ ሆና ብቅ ብላለች ።

በዓለም ዋንጫ መጀመሪያዎቹ አሥርት ዓመታት አፍሪካ በቅኝ አገዛዝ እና በፊፋ የኮታ መድብ ኢ-ፍትሃዊነት ምክንያት የመሳተፍ ዕድሏ በጣም ጠባብ ነበር።

ይሁን እንጂ እ.አ.አ በ1934 በጣልያን በተካሄደው ሁለተኛው የዓለም ዋንጫ ግብፅ ተሳትፎ በማድረግ  የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ሀገር በመሆን ታሪክ ሰራች።


 

በወቅቱ ከሀንጋሪ ጋር ተጫውታ 4 ለ 2 በሆነ ውጤት ብትሸነፍም የአፍሪካን ስም በዓለም መድረክ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስጠራች ሀገር ሆና ተመዝግባለች።

አብዱልራህማን ፋውዚ በጨዋታው ለግብጽ ሁለቱንም ግቦች በማስቆጠር በዓለም ዋንጫው ግብ ማስቆጠር የቻለ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ተጫዋች ሆኗል።

አብዱልራህማን ፋውዚ በዚህ ጨዋታ ላይ ሶስተኛ ግብ አስቆጥሮ የነበረ ቢሆንም፣ ዳኛው በስህተት ከጨዋታ ውጪ (Offside) በማለት ሽረውታል።

 ያ ግብ ቢጸድቅ ኖሮ በዓለም ዋንጫ ታሪክ የመጀመሪያውን ሀትሪክ (በአንድ ጨዋታ ሶስት ግብ) ያስቆጠረ አፍሪካዊም ይሆን ነበር።

ከዚያ በኋላ አፍሪካ ወደ መድረኩ ዳግም ለመመለስ እስከ 1970 (እ.አ.አ) መጠበቅ ነበረባት።


 

ሞሮኮ እ.አ.አ በ1970 በሜክሲኮ አስተናጋጅነት በተካሄደው ዘጠነኛ የዓለም ዋንጫ በመሳተፍ ከግብጽ ቀጥሎ ሁለተኛዋ የአፍሪካ ሀገር ሆናለች።

እ.አ.አ በ1978 በአርጀንቲና የተካሄደው 11ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ አፍሪካ ታሪክ የጻፈችበት ነበር።

በውድድሩ ላይ የተሳተፈችው ቱኒዚያ ሜክሲኮን 3 ለ 1 በማሸነፍ የአፍሪካን የዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ድል አስመዝግባለች።

እ.አ.አ በ1982 በስፔን አስተናጋጅነት በተካሄደው 12ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ ተሳትፋ የነበረችው አልጄሪያ በወቅቱ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን የነበረውን ጀርመንን (በወቅቱ ምዕራብ ጀርመን) 2 ለ 1 በማሸነፍ ያስመዘገበችው ውጤት ዓለም ያልጠበቀው ነበር።

በጣልያን እ.አ.አ በ1990 በተካሄደው 14ኛው የዓለም ዋንጫ ካሜሮን በመጀመሪያ ጨዋታዋ አርጀንቲናን 1 ለ 0 ያሸነፈችበት ድል በእግር ኳስ አፍቃሪያን ላይ ግርምትን የፈጠረ ክስተት ሆኖ አልፏል።


 

ታዋቂው የካሜሮን አጥቂ ሮጀር ሚላ በ38 ዓመቱ ግብ በማስቆጠር አንጋፋው የአፍሪካ ተጫዋች መሆን ችሏል።

ካሜሩን በወቅቱ የሩብ ፍፃሜ (Quarter-finals) ደረጃ ላይ በመድረስ የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ሀገር በመሆን ታሪክ ሰራች።

የማይበገሩት አንበሶች በወቅቱ በሩብ ፍጻሜ በእንግሊዝ 3 ለ 2 ተሸንፈው ግማሽ ፍጻሜ መግባት ባይችሉም በውድድሩ ላይ ስኬታማ ግስጋሴ አድርገዋል።

እ.አ.አ በ2002 በጃፓን እና ኮሪያ ሪፐብሊክ ጣምራ አዘጋጅነት የተካሄደው 17ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ተካሄዷል።

ሴኔጋል በመጀመሪያ ጨዋታዋ የወቅቱን የውድድሩን አሸናፊ ፈረንሳይ (የ1998 ሻምፒዮን) 1 ለ 0 በመርታት ያስመዘገበችው ድል ዓለምን ጉድ አሰኝቷል።

ፓፓ ቡባ ዲዮፕ ግቧን ያስቆጠረው ተጫዋች ነው። 

ሴኔጋል በፈረንሳይ ድል ሳትገታ እስከ ሩብ ፍጻሜ መጓዝ ብትችልም በቱርኪዬ 1 ለ 0 ተሸንፋ አራት ውስጥ መግባት አልቻለችም።

እ.አ.አ በ2010 ደቡብ አፍሪካ 19ኛውን የፊፋ ዓለም ዋንጫ ያዘጋጀች ሲሆን ይህም በአፍሪካ ምድር የተካሄደ የመጀመሪያው ዓለም ዋንጫ መሆኑ አዲስ ታሪክ እንዲጻፍ አስችሏል።

ጋና አህጉሪቱን ወክላ እስከ ሩብ ፍፃሜ ብትጓዝም በኡራጓዩ ተጫዋች ሉዊስ ሱዋሬዝ የዕጅ ኳስ ጥፋትና በጭማሪ ሰዓት በባከነ ፍፁም ቅጣት ምት ምክንያት ለግማሽ ፍፃሜ ሳትበቃ ቀርታለች።

በጋና እና ኡራጓይ መካከል የተደረገው ጨዋታ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አንድ ለአንድ ተጠናቆ ነበር። ይህን ተከትሎ 30 ደቂቃ ተጨመረ።

የጭማሪው ሰዓት ሊያልቅ ጥቂት ሰከንዶች ብቻ ሲቀሩ (በ120ኛው ደቂቃ ላይ) ጋና ድንቅ የማጥቃት እንቅቃሴ አድርጋለች። የጋናው ተጫዋች ዶሚኒክ አዲያህ በግንባሩ የገጫት ኳስ ወደ ኡራጓይ መረብ ውስጥ እየገባች ሳለ፣ የኡራጓዩ አጥቂ ሉዊስ ሱዋሬዝ (Luis Suárez) ልክ እንደ ግብ ጠባቂ በመዝለል ኳሷን በሁለት እጆቹ  በመንካት አወጣት።

ይህንን ተከትሎ ዳኛው ለሱዋሬዝ የቀይ ካርድ በመስጠት ከሜዳ  ሲያሰናብቱት፣ ለጋና ደግሞ ወሳኝ የፍፁም ቅጣት ምት (Penalty) ሰጡ።


 

መላው የአፍሪካ አህጉር እና ስታዲየሙ ውስጥ የነበሩ ደጋፊዎች ታሪክ ሊሰራ መሆኑን እርግጠኛ ሆነው ጨፈሩ። ፍፁም ቅጣት ምቱን ለመምታት የጋናው ኮከብ አሳሞአ ጊያን ቀረበ። ነገር ግን የመታው ኳስ የጎሉን አግዳሚ  (Crossbar) መትቶ ወደ ውጪ ወጣ።

በዚህ ሰዓት ቀይ ካርድ አይቶ ወደ መልበሻ ክፍል እየተጓዘ የነበረው ሉዊስ ሱዋሬዝ፣ ኳሷ መውጣቷን ሲያይ በደስታ ሲዘልና ሲጨፍር በካሜራ ታይቷል። ይህ ድርጊቱ ለአፍሪካውያን ትልቅ ቁጭትና ንዴት የፈጠረ ነበር።

ጨዋታው 1 ለ 1 በሆነ ውጤት ተጠናቆ ወደ መለያ ምት ሲያመራ፣ ጋና 4 ለ 2 በሆነ ውጤት ተሸነፈች። ኡራጓይ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ስትሰናዳ፣ የጋና እና የመላው አፍሪካ የዓለም ዋንጫ ህልም ሳይሳካ ቀረ።

ይህ ክስተት የጋናን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያን ልብ የሰበረ ነበር።

አፍሪካውያን በዚህ ክስተት አንገታቸውን ደፍተው አልቀሩም። እ.አ.አ በ2022 በኳታር አስተናጋጅነት በተካሄደው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ሞሮኮ ተአምር ሰሪ ሀገር ሆነች።

የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን (የአትላስ አንበሶች)  ሳይጠበቁ ስፔንን እና ፖርቱጋልን አሸንፈው በዓለም ዋንጫ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ግማሽ ፍፃሜ (Semi-final)  ደረሱ። ይህም ሞሮኮ ለዓለም ዋንጫ ፍጻሜ የገባች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ሀገር በመሆን አዲስ ታሪክ እንድትጽፍ አስችሏታል።

በግማሽ ፍጻሜው በፈረንሳይ እንዲሁም በደረጃ ጨዋታው በክሮሺያ ተሸንፋ አራተኛ ደረጃን ይዞ ብታጠናቅቅም አፍሪካን ያኮራ ደማቅ ታሪክ ጽፋለች።

ይህ የሞሮኮ ድል የአፍሪካውያንን የይቻላል መንፈስ ከፍ ያደረገ ክስተት ሆኗል።


 

በውድድሩ የ96 ዓመታት ታሪክ የዘንድሮውን ጨምሮ 14 የአፍሪካ ሀገራት በዓለም ዋንጫው ላይ ተሳትፈዋል።

ካሜሮን ስምንት ጊዜ በመሳተፍ ቀዳሚውን ስፍራ ይዛለች።

ሞሮኮ እና ቱኒዚያ በተመሳሳይ ሰባት ጊዜ ተሳትፎ አድርገዋል።

ናይጄሪያ ስድስት ጊዜ በመድረኩ ላይ ስትሳተፍ አልጄሪያ እና ጋና በተመሳሳይ አምስት ጊዜ የመሳተፍ እድል አግኝተዋል።

ግብጽ፣ ሴኔጋል፣ ኮትዲቯር እና ደቡብ አፍሪካ በተመሳሳይ አራት ጊዜ ተሳትፎ ሲያደርጉ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አንድ ጊዜ ተሳትፋለች።

አንጎላ፣ ቶጎ እና ኬፕቨርዴ በተመሳሳይ የአንድ አንድ ጊዜ ተሳትፎ ያላቸው ሀገራት ናቸው።

የደሴቲቷ ሀገር በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ታሪካዊ ተሳትፎዋን የምታደርግ ሲሆን ይህም በውድድሩ የተሳተፈች 14ኛ ሀገር ያደርጋታል። 

23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ ጣምራ አዘጋጅነት  እየተካሄደ ይገኛል።

በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 10 የአፍሪካ ሀገራት ይሳተፋሉ።

በዚህም መሰረት ሞሮኮ፣ ሴኔጋል፣ ግብፅ፣ ኮትዲቯር፣ አልጄሪያ፣ ቱኒዚያ፣ ጋና፣ ኬፕቨርዴ እና ደቡብ አፍሪካ በቀጥታ ያለፉ የአፍሪካ ሀገራት ናቸው።

በአንጻሩ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብሔራዊ ቡድን በክፍለ አህጉራዊ የማጣሪያ ውድድር (Play-off) የጃማይካ አቻዋን በመርታት ለዓለም ዋንጫው ያለፈች 10ኛዋ የአፍሪካ ሀገር በመሆን አዲስ ታሪክ ሰርታለች።

ዛሬ አፍሪካ  በዓለም ዋንጫ ላይ ዝም ብላ "ለመሳተፍ" ብቻ ሳይሆን፣ ዋንጫውን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አፍሪካ ምድር ለማምጣት በፅናት ለመፋለም ተዘጋጅታለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም