ቀጥታ፡

የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና ጥራቱን ለማስጠበቅ የተከናወኑ ተግባራት የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እያሳደጉ ነው

ሃዋሳ፤ ሰኔ 11/2018(ኢዜአ)፦ የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና ጥራቱን ለማስጠበቅ የተከናወኑ ተግባራት ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እያሳደጉ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ በቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎች የቨርሚ ኮምፖስት ዝግጅትና በቡና ክላስተር አጠቃቀም ላይ ያተኮረ የልምድ ልውውጥ መድረክ በሃዋሳ ከተማ አካሂዷል።


 

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) እንደገለጹት የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና የቡና ጥራትን ለማስጠበቅ የተከናወኑ ተግባራት በዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እያሳደጉት ነው።

ባለፉት ዓመታት በቡና ግብይት ስርአት ውስጥ የተደረጉ ሪፎርሞች ተጨባጭ ውጤት ማምጣታቸውን ጠቅሰው፣ የሪፎርም ሥራው የቡና ተፈጥሯዊ ጣዕም እንዲጠበቅና ገዢዎች ምርቱን በቀጥታ እንዲያገኙ አስችሏል ብለዋል።

በዚህም ለዓለም ገበያ የሚቀርበው የቡና መጠንና ጥራት እያደገ መምጣቱን ጠቁመው፣ በዘንድሮው የምርት ዘመን ለዓለም ገበያ ከሚቀርበው ቡና 3 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ዘንድሮ በዓለም ገበያ የቡና ዋጋ ቢወርድም የኢትዮጵያ ቡና ጥራት ደረጃ ጥሩ በመሆኑ በዓለም ገበያ ከአምናው በተሻለ ዋጋ መሸጡን ተናግረዋል።

በመሆኑም የቡና ጥራትን ለማስጠበቅና ምርትና ምርታማነትን ይበልጥ ለማሳደግ በየአካባቢው ያሉ ምርጥ ተሞክሮዎችን የመቀመር ሥራ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የዛሬው መድረክም በሲዳማ ክልል በቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎችና በአርሶ አደር ማሳ የሚከናወነውን የቨርሚ-ኮምፖስት አዘገጃጀት ተሞክሮን በማስፋት በዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

የሲዳማ ክልል ቡና፣ ፍራፍሬና ቅመማቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መስፍን ቃሬ በበኩላቸው በክልሉ የቡና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግና ጥራቱን ለማስጠበቅ የአፈር ለምነት የመጠበቅ ሥራ እየተሰራ ነው።


 

በተለይም የተፈጥሮ ማዳበሪያ ላይ በማተኮር በቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎችና በአርሶ አደሮች ማሳ ቨርሚ ኮምፖስት የማዘጋጀት ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በዚህም ባለፉት ሁለት ዓመታት 220 የቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎች ቨርሚ ኮምፖስት በማዘጋጀት ለቡና አምራች አርሶ አደሮች እያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል።

የቨርሚ ኮምፖስት የቡና ምርታማነትና ጥራትን በመጨመር መሬቱ ተከታታይ ምርት እንዲሰጥ ከማድረግ ባሻገር የአካባቢ ብክለትን በመቀነስ ጉልህ ድርሻ አለው ነው ያሉት።

የክልሉ መንግስት የተገኘውን ተሞክሮ በማስፋት የቡና ምርትና ምርታማነትን የማሳደግና ጥራቱን የማስጠበቅ ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም አክለዋል።

በመድረኩ ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ የቡና ማዘጋጃ ኢንደስትሪዎች ተወካዮች፣ አርሶ አደሮችና የምርምር ተቋማት የተገኙ ሲሆን የሲዳማ ክልል ምርጥ ተሞክሮም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በቀጣይም በአርሶ አደር ማሳ እና በቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎች የመስክ ምልከታና የልምድ ልውውጥ እንደሚደረግ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም