ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲው በምርምርና በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት የጀመረውን ቅንጅታዊ አሰራር ያጠናክራል

ወላይታ ሶዶ፤ ሰኔ 11/2018 (ኢዜአ)፡-ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በምርምር ሥራዎችና በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የጀመረውን ቅንጅታዊ አሰራር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ።

በዩኒቨርሲቲው በምርምር ፕሮጀክቶች እና በማህበረሰብ አገልግሎቶች የተከናወኑ ተግባራትን ለመገምግምና ቅንጅታዊ ሥራን ለማጠናከር ያለመ መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጉቼ ጉሌ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ ዩኒቨርሲቲው በምርምር ሥራዎችና በማህበረሰብ አገልግሎት የአካባቢውን ማህበረሰብ በተሻለ መልኩ ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ አስቀምጦ እየሰራ ነው። 

በተለይ ችግር ፈቺ የምርምር ውጤቶችን እውን ለማድረግና ዓለም አቀፍ ዕድሎችን አስፍቶ ለመጠቀም የተመራማሪዎችን አቅም ማሳደግ ላይ አተኩሮ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ለእዚህም የምርምር ስራዎቹንና የማህበረሰብ አገልግሎቶቹን ለማጎልበት ከአገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ መሰል ተቋማት ጭምር ትብብርና ትስስሩን ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ ተመራማሪዎችን አቅም በማሳደግና ከዓለም አቀፍ መሰል ተቋማት ጋር ትስስሩን በማጎልበት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመረው ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ዘውድነህ ቶማስ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው በምርምርና በማህብረሰብ አገልግሎቶች ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ ነው። 


 

በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ ከ84 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ 54 የምርምር ሥራዎችን እንዲሁም 70 የማህበረሰብ አገልግሎቶችን ማከናወኑን ጠቁመዋል።

በዚህም ከ1 ሚሊዮን በላይ የአካባቢውን ማህበረሰብ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡

የዛሬው መድረክም የተለያዩ ምርምሮች ውጤታማነትን በጋራ ገምግሞ የተሻለ አቅጣጫ ለመያዝና ለቀጣይ ዓመት መሰል ሥራዎች ተሞክሮ ለመቀመር ጠቃሚ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ ተመራማሪዎች እና መምህራን ተገኝተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም