ቀጥታ፡

የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አቅመ ደካሞችን ከመደገፍ ባሻገር ሀገራዊ ልማትን በማፋጠን በኩል የጎላ ሚና አለው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2018(ኢዜአ)፦ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አቅመ ደካሞችን ከመደገፍና ሀገራዊ ልማትን ከማፋጠን ባለፈ በሕዝቦች መካከል ጠንካራ ማህበራዊ ትስስርን የመፍጠር ፋይዳ እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዘንድሮውን የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በኦሮሚያ ክልል በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ ጎሮ ወረዳ ዛሬ በይፋ አስጀምረዋል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ የማስጀመሪያ ወቅት እንደተናገሩት፤ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አቅመ ደካሞችን ከመደገፍና ሀገራዊ ልማትን ከማፋጠን ባለፈ በህዝቦች መካከል ጠንካራ ማህበራዊ ትስስርን የመፍጠር ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በዋናነት የአቅመ ደካማና የእጅ አጠር ወገኖችን ቤት የመጠገን፣ የማደስና አዳዲስ የመኖሪያ ቤቶችን የመገንባት ስራዎችን ያካትታል ብለዋል።

እንዲሁም ሀገር በቀልና የፍራፍሬ ችግኞችን በመትከል የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች በትኩረት እንደሚከናወኑም አክለዋል።

በተጨማሪ በሕዝብ አቅም የሚገነቡ፣ ቀበሌን ከቀበሌ እንዲሁም ሰፈርን ከሰፈር የሚያገናኙ የገጠር መንገዶች፣ መለስተኛ ድልድዮች፣ ፋርማሲዎችና የጤና ኬላዎች እንደሚገነቡም ተናግረዋል።

ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት 35 ሺህ የሚጠጉ የሙዓለ ህጻናት ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ከ4 ሚሊየን በላይ ህጻናት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።

ይህም ህጻናት ወደ አንደኛ ደረጃ ከመሸጋገራቸው በፊት መሰረታዊ እውቀትን፣ ባህልንና ማህበራዊ ግንኙነትን ቀስመው እንዲያድጉና የትምህርት ማቋረጥ ምጣኔን ለመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገር ብልጽግና በመንግስት በጀትና የገንዘብ አቅም ብቻ ሊረጋገጥ እንደማይችልም ነው የተናገሩት።

ብልጽግና የሚረጋገጠው የሕዝቡን ጉልበት፣ ሀብት፣ እውቀት ከመንግሥት ዕቅዶች ጋር አሰናስሎ መጠቀም ሲቻል መሆኑን ጠቁመው በርካታ ችግሮችን መፍታት ያስችላልም ነው ያሉት።

የሚሰራ እጅ፣ የሚናገር አፍና የሚያስብ አእምሮ በጋራ ሲሰናሰሉ ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉም ተናግረዋል።

የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ20 እስከ 30 ሚሊየን የሚደርስ ሕዝብ የሚሳተፍበት ትልቅ ሀገራዊ ንቅናቄ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወጣቶች ይህንን አጋጣሚ ሊጠቀሙ ይገባል ብለዋል።


 

በዚህም በቤት እድሳት፣ በችግኝ ተከላና በእርሻ ስራዎች ላይ አሻራቸውን እንዲያሳርፉም ጥሪ አቅርበዋል።

አዛውንቶችም በሂደቱ ውስጥ ለወጣቱ ትውልድ ባህልን፣ ቋንቋንና ስርዓትን በማስተማር የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ከፊታችን ያለው ዘመን መሰረታዊ የሆኑ የኢትዮጵያ ችግሮች የሚፈቱበትና ከፍተኛ ስራ የሚጠይቅ በመሆኑ መላው ሕዝብ በዚህ የክረምት ወቅት ጊዜውን በአግባቡ በመጠቀም ለኢትዮጵያ ብልጽግና የበኩሉን እንዲወጣም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም