የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ጀምሮ ለሚያካሂደው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የሚያደርገውን ዝግጅት አጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ጀምሮ ለሚያካሂደው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የሚያደርገውን ዝግጅት አጠናክሮ ቀጥሏል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ጀምሮ ለሚያካሂደው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የሚያደርገውን ዝግጅት አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
ለዚህም በዛሬው ዕለት ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ አመካካሪዎች ያዘጋጀውን የግንዛቤና የክህሎት ሥልጠና መስጠት ጀምሯል።
በአዲስ አበባ እየተካሄደ የሚገኘው ይህ የአመካካሪዎች ሥልጠና ከዛሬ ሰኔ 11 እስከ 17 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ለሰባት ተከታታይ ቀናት እንደሚቆይ ተጠቁሟል።
በሥልጠናው መክፈቻ ላይ የተገኙት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እንደገለጹት፤ ይህ የሥልጠና መርሃ ግብር ልዩነቶች በምክክር የሚፈቱበት፣ በግልጽነትና በመግባባት የሚቀረፉባት ኢትዮጵያን ለመገንባት በጋራ በሚደረገው ጉዞ ላይ ሌላ አንድ ትልቅ ምዕራፍና ስኬት ነው።
አመካካሪዎች ይህን ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት በታማኝነት የሚሸከሙ ባለአደራዎች መሆናቸውን የጠቀሱት ፕሮፌሰሩ፤ ራሳቸውን የሀገሪቱን ማኅበራዊ፣ ሕዝባዊና ዴሞክራሲያዊ መጻኢ ዕድል በጋራ የሚገነቡ ታሪክ ሠሪዎች አድርገው ማየት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
ይህ ሥልጠና አመካካሪዎች የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ክብር የሚጠብቁ እንዲሁም ለሰላም፣ ለፍትሕና ለአንድነት ያላቸውን የጋራ ምኞት የሚያሳኩ ምክክሮችን መምራት የሚያስችላቸውን ዕውቀት፣ ክህሎትና እሴት ለመጨበጥ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
አመካካሪዎች በጉባኤው ወቅት ሁሉም ተሳታፊዎች እኩል የመናገርና የመሳተፍ ዕድል እንዳላቸው ማረጋገጥ፣ በውይይት ወቅት የሚነሱ አለመግባባቶችን በአግባቡ መምራት እንዲሁም ውይይቱ ወደ ጋራ መግባባት እንዲያመራ መንገድ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
አመካካሪዎች ይህንን ትልቅ ሀገራዊ አደራ በትሕትና፣ በገለልተኝነት እና በትዕግሥት እንዲወጡትም አደራ ብለዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤል ዶ በበኩላቸው አመካካሪዎች በሒደት ውስጥ የሚነሱ ልዩ ልዩ ስሜቶችን በአግባቡ መረዳትና መለየት መቻል ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።
ስሜቶችን በጥንቃቄ በማስተናገድም ወደ ገንቢ የጋራ ተሳትፎ እንዲቀየሩ መርዳት የአመካካሪዎች ዋነኛ ሚና ሊሆን እንደሚገባም ነው አፅንኦት የሰጡት።
በኢትዮጵያ የስዊድን ኤምባሲ ምክትል ኃላፊ ሄድቪግ ሎህም ለምክክሩ ስኬታማነት ስዊድን የበኩሏን እየተወጣች መሆኑን ገልጸዋል።
የሒደቱ አካል የሆኑት አመካካሪዎች በጉባኤው ወቅት ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን በቁርጠኝነት መውጣት አለባቸው ብለዋል።