የህዝብ እና የመንግስት ሥራ ሲደመር የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ ይቻላል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የህዝብ እና የመንግስት ሥራ ሲደመር የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ ይቻላል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2018 (ኢዜአ):- ህዝቡ የሚያከናውናቸው ሥራዎች ከመንግሥት ጥረቶች ጋር ሲደመሩ፣ የሚፈለገውን የሀገር ብልጽግና ማረጋገጥ እንደሚቻል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዘንድሮውን የክረምት የበጎ ፈቃድ ዘመቻ ዛሬ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ ጎሮ ወረዳ በይፋ አስጀምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተከናወኑት የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራዎች በርካታ ውጤቶች ማስገኘታቸውን ገልጸዋል።
በበጎ ፈቃድ ሥራው ውስጥ ከሚካተቱት ዋና ዋና ተግባራት መካከል የቤት ግንባታ (ሃውሲንግ) አንዱ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚህም የእጅ አጠር ሰዎችን ቤት የመጠገን፣ የማደስና የመሥራት ሥራ እንደሚከናወን አስታውቀዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ሀገር በቀል ዛፎችን መትከል፣ የገጠር መንገዶችና መለስተኛ ድልድዮችን በሕዝብ አቅም መገንባት እንዲሁም ፋርማሲዎችንና የመዋዕለ ሕፃናት ትምህርት ቤቶችን መገንባት የዚሁ የበጎ ፈቃድ ሥራ አካል መሆናቸውን አብራርተዋል።
በእነዚህ ሁሉ የልማት ሥራዎች ውስጥ በመንግሥት በጀት የማይሸፈኑ፣ ነገር ግን የማኅበረሰቡን የዕለት ተዕለት ችግሮች መፍታት የቻሉ በርካታ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።
አምና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እንደተደረገው ሁሉ፣ ዘንድሮም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ወሊሶ ላይ መጠነኛ ቤቶችን እንደሚገነባ ገልጸው፤ በወልቂጤ፣ ስልጤ፣ ወራቤና ሐዲያ ዞኖች እንዲሁም በከምባታ ላይ ሕዝቡና የመንግሥት አካላት የቤት ግንባታ ሥራውን እያሰፉ በመምጣታቸው በአካባቢው ላይ የሚጨበጡ ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቁመዋል።
ተስፋችን በሁሉም ክልሎችና ዞኖች የሚገኘው እያንዳንዱ ማኅበረሰብ ተባብሮ የእጅ አጠር ሰዎችን ቤት እንዲሠራ፣ ትምህርት ቤቶችን እንዲገነባ፣ በየአካባቢው አቅም የሚገነቡ መንገዶችንና የጤና ኬላዎችን እንዲያቆም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሕዝቡ የሚሠራው ሥራ ከመንግሥት ጋር ሲደመር የሚፈለገውን ብልጽግና ማረጋገጥ እንደሚቻልም ነው ያስገነዘቡት።
የኢትዮጵያ ሀብቷ ሕዝቧ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሕዝቡ በሚሰበሰብበት ወቅት ጉልበቱን፣ ሀብቱንና ዕውቀቱን በመደመር በጣም በርካታ ችግሮችን መፍታት እንደሚችል አስረድተዋል።
በአጠቃላይ የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች የሚሳተፉበት፣ ገንዘብና ሀብት የሚፈስበት እንዲሁም ጉልበት የሚወጣበት ትልቅ የትብብር መገለጫ መሆኑንም አክለዋል።
ባለፉት ዓመታት የተገነቡት 35 ሺህ መዋዕለ ሕፃናት በመንግሥት ሳይሆን በሕዝቡ ተሳትፎ የተከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመው፣ እነዚህ መዋዕለ ሕፃናት ሀገርን የሚረከብ ትውልድ ለመገንባት መሠረት የሚጣልባቸው መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
አያይዘውም የማይሠራ እጅ በሚናገር አፍ ፍሬ አያፈራም፤ የሚሠራ እጅ በሚናገር አፍና በሚያስብ ጭንቅላት የተደገፈ እንደሆነ ግን ብልጽግና ይረጋገጣል ብለዋል።
የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራዎች ከበጀትና ከልማት በላይ መሆናቸውን ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሥራዎቹ ዜጎችን የሚያስተሳስሩ፣ የሚያስተባብሩ፣ የሚያዋህዱ፣ የሚያስተዋውቁና መልካም ሥራዎችን መሥራት የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ወጣቶች በእነዚህ በጎ ፈቃድ ሥራዎች ላይ በስፋት በመሳተፍ፣ አረጋውያንም መልካም እሴቶችን በማስተማር የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ መፍጠር እንችላለን ነው ያሉት።
ከሥራና ከብርታት ውጪ የሚገነባ ሀገር እንደሌለ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ተባብረን ከሠራን በታሰበው መንገድ የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ እንደሚቻል ምንም ጥርጥር የለውም ብለዋል።
ከፊታችን ያለው ዘመን ብዙ ድካም፣ ብዙ ሥራና ከፍተኛ ውጤት የሚጠበቅበት መሆኑንና መሠረታዊ የሚባሉ የኢትዮጵያ ችግሮች መልክ የሚይዙበት ወቅት በመሆኑ፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ ሁሉም በጋራና በትብብር ቆሞ ሥራውን እንዲሠራ አደራ ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ክረምቱን እንጠቀምበት፣ ዝናቡን እንጠቀምበት፣ ጊዜውን እንጠቀምበት፤ ለኢትዮጵያ ብልጽግና አንዳንድ ጡብ የምናኖርበት መልካም ዜጎች ያድርገን ሲሉም አክለዋል።