የአብሮነት እሴቶችን ለሰላም ግንባታ በማዋል በህዝቦች መካከል መቻቻልና መቀራረብን ማጎልበት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የአብሮነት እሴቶችን ለሰላም ግንባታ በማዋል በህዝቦች መካከል መቻቻልና መቀራረብን ማጎልበት ይገባል
ሀዋሳ፤ ሰኔ 11/2018(ኢዜአ)፦ የአብሮነት እሴቶችን ለሰላም ግንባታ በማዋል በህዝቦች መካከል መቻቻልና መቀራረብን ማጎልበት እንደሚገባ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) ገለጹ።
"የሚዲያ ተቋማት ሚና ለሰላም ግንባታ" በሚል መሪ ሀሳብ ሰላም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ጋር በመተባበር በሀዋሳ ከተማ ከመገናኛ ብዙሃን አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታው ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) እንዳሉት ሰላምን ለማጽናት የሚዲያ ተቋማት ያላቸው ሚና ላቅ ያለ ነው።
እንደ ሀገር እሴቶቻችንን ለሰላም ግንባታ በማዋል በህዝቦች መካከል መቻቻልና መቀራረብን ማጎልበት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ለእዚህም መገናኛ ብዙሃን ትክክለኛ መረጃዎችን ለህዝብ ተደራሽ በማድረግ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠርና ሰላምን በዘላቂነት ለማጽናት ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በውጤታማነት እንዲጠናቀቅ መገናኛ ብዙሃን ያበረከቱት አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ግዛው ተስፋዬ በበኩላቸው መገናኛ ብዙኃን ሀሰተኛ መረጃን በማጥራት ትክክለኛ መረጃ ለህዝብ ማድረስ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የህግ ጥሰቶች ሲያጋጥሙም አስተማሪ በሆነ መንገድ መረጃ መስጠት አለባቸው ብለዋል።
በመድረኩ ከሲዳማ፣ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ከደቡብ ኢትዮጵያና ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች የመገናኛ ብዙሃን አመራሮችና ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።