ቀጥታ፡

በሸገር ከተማ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል

ሸገር፤ ሰኔ 11/2018(ኢዜአ)፦ በሸገር ከተማ በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች ለመትከል ዝግጅት መደረጉን የከተማ አስተዳደሩ ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ደጀኔ በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከዚህ ቀደም በተከናወኑ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሮች የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል፣ ለአፈርና ውሃ ጥበቃ እንዲሁም ለሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች ተገኝተዋል።


 

መርሃ ግብሩ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምርም ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።

በ2015 ዓ.ም የከተማው የደን ሽፋን 11 በመቶ ብቻ እንደነበረ አስታውሰው ኅብረተሰቡን በማሳተፍ በተከናወኑ ሥራዎች በአሁኑ ወቅት የደን ሽፋኑን 21 በመቶ ማድረስ ተችሏል ብለዋል።

በዘንድሮው መርሃ ግብር ለከተማዋ የአየር ንብረት ተስማሚ ለሆኑ የፍራፍሬ ዓይነቶች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱንም አስታውሰዋል።

በዚህም መሠረት እንደ አፕል፣ አቮካዶ፣ ብርቱካን እና ሎሚ ያሉ የፍራፍሬ ችግኞች በስፋት ለተከላ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ1 ሺህ 200 ሄክታር በላይ መሬት ላይ የፍራፍሬ ችግኞች ብቻ ለመትከል የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት የከተማዋ ነዋሪዎች በመኖሪያ አካባቢያቸው የፍራፍሬ ችግኞችን ተክለው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተከታታይ ሥልጠናዎች ሲሰጡ መቆየታቸውንም ጠቁመዋል።


 

በአሁኑ ወቅት ኅብረተሰቡ ከመንግሥት ጋር በመሆን በመንግሥትና በግል ይዞታዎች፣ እንዲሁም ለፍራፍሬና ለውበት ተስማሚ በሆኑ ቦታዎች ላይ የችግኝ መትከያ ጉድጓዶችን በማዘጋጀት ላይ ይገኛልም ነው ያሉት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም