ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በክረምት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ይተከላሉ

ወላይታ ሶዶ፤ ሰኔ 11/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በክረምት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። 

አረንጓዴ ዐሻራ መርሀግብር የተፈጥሮ ሚዛንን ለመጠበቅ ካለው ፋይዳ ባለፈ የምግብ ዋስትናንና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ታላቅ ሀገራዊ ግብንም ይዟል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልልም ካለፉት ሰባት ዓመታት ወዲህ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀግብርም ለችግኝ ተከላ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ በመከናወኑ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መጥቷል።

በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል እና የተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ ኃላፊ አንደኛ ሽናሌ እንደገለጹት፣ በክልሉ የተፈጥሮ ሚዛኑን የጠበቀ አረንጓዴ አካባቢን ዕውን በማድረግ በኩል ውጤት ተገኝቷል፡፡


 

በተለይ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ባለፉት ሰባት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት የተራቆተ መሬትን መልሶ በደን በመሸፈንና ምርታማነትን በማሳደግ በኩል ለውጥ መታየቱን ተናግረዋል።

በዘንድሮ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብርም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ አስፈላጊው ዝግጅት በማድረግ ወደ ተግባር መገባቱን ነው የገለጹት።

በዘንድሮ የበልግ ወቅትም የደን፣ የፍራፍሬ እና ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸው ችግኞች መተከላቸውን ኃላፊው አስታውሰዋል።    

ዘንድሮም ለመርሐ-ግብሩ ስኬት በተሰጠው ልዩ ትኩረት፤ በበልግ ወቅት ከተተከሉት በተጨማሪ በክረምት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተለያየ ጥቅም የሚሰጡ ችግኞች ለመትከል አስፈላጊው ቅድመ ዘግጅት መደረጉን አስታውሰዋል።

ለእዚህም በክልሉ ባሉ ከ1ሺህ 200 በላይ ችግኝ ጣቢያዎች ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚሰጡ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ነው የገለጹት።

ችግኞቹ ለምግብነት የሚውሉ፣ የፍራፍሬ፣ ለጥምር ደን፣ ለውበትና ለጥላ ዛፍ የሚያገለግሉ መሆናቸውን ገልጸው፣ ለእንስሳት መኖ የሚውሉም መተከላቸውን ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀግብር ለችግኝ ተከላ የሚሆኑ ጉድጓዶችን በመቆፈር ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ባለፉት ሰባት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ590 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን በዚህም የክልሉ የደን ሽፋን ከነበረበት 18 ነጥብ 9 ከመቶ በአሁኑ ወቅት ወደ 23 በመቶ መድረሱ ታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም