ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከ2 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ተገኝቷል

ደብረ ብርሃን፤ ሰኔ 11/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በዘንድሮው በጋ መስኖ ከለማው ስንዴ ከ2 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ማግኘቱ ተገልጿል።

በዞኑ ግብርና መምሪያ የመስኖ አጠቃቀም አግሮኖሚስት ዘሩ ገረመው እንደገለጹት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አርሶ አደሩ በምግብ ራሱን ከመቻል ያለፈ ምርት እንዲያመርት አስችሏል።

በበጋው ወራት የተለያዩ የመስኖ አማራጮችን በመጠቀም 51 ሺህ 966 ሄክታር መሬትን በስንዴ በማልማት ከ2 ሚሊየን 147 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ማግኘት መቻሉን ገልጸዋል።

ምርታማነቱን ለማሳደግም በባለሙያዎች ድጋፍ የማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘርና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን አርሶ አደሩ በአግባቡ እንዲጠቀም ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።

በዚህም የዞኑ የበጋ መስኖ ስንዴ ምርታማነት በሄክታር በአማካይ 60 ኩንታል እንዲደርስ ማስቻሉን አስረድተዋል።


 

አርሶ አደሮቹ ያመረቱትን ስንዴ ከቤት ውስጥ ፍጆታ ባሻገር ለኢንዱስትሪዎች ግብዓትና ለአካባቢው ገበያ በማቅረብ የገበያ ማረጋጋት ስራ ማከናወናቸውን ተናግረዋል።

በዞኑ የንግድና ገበያ ልማት መምሪያ የሰብልና ኢንዱስትሪ ግብይት ባለሙያ ጌታው ሙሉ፤ በዞኑ በዘንድሮው በጋ በጥራትና በብዛት ስንዴን በማምረት ለገበያ እየቀረበ ነው ብለዋል።

እስካሁንም 200 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ የስንዴ ምርት በአካባቢው ለሚገኙ አንዱስትሪዎችና ሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት መቅረቡን ጠቁመው የገበያ ማረጋጋቱ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በዚህም አሁን ላይ የስንዴ ዋጋ መቀነሱን ጠቁመው ይህም የዱቄት ፋብሪካዎች በቂ ዱቄት በማምረት ለዳቦ አምራቾች እንዲያቀርቡ እድልን ፈጥሯል ብለዋል።

በዞኑ በሲያደብርና ዋዩ ወረዳ አርሶ አደር ታፈሰ ቱሉ፤ የበጋ መስኖ ልማት ስራ ምርታማነታችንን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ሃብት እንድንፈጥር አስችሎናል ነው ያሉት።

በዘንድሮው በጋም አራት ተኩል ሄክታር ማሳቸው ላይ ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር በመተባበር ስንዴን በኩታ ገጠም በማልማት ከ200 ኩንታል በላይ ምርት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ያመረቱትን ምርትም በተፈጠረላቸው የገበያ ትስስር በአካባቢው ለሚገኙ አንዱስትሪዎች በማቅረብ የተሻለ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ሌላው የዚሁ ወረዳ አርሶ አደር ደርቤ ፈለቀ በበኩላቸው አንድ ሄክታር ማሳቸውን በበጋ ስንዴ በማልማት 60 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም