ቀጥታ፡

ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ድጋፋችንን አጠናክረን ቀጥለናል - የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሃደ ሲንቄዎች

ሮቤ፣ ሰኔ 11/2018 (ኢዜአ)፦ ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት እያደረጉት ያለውን ሁለንተናዊ ድጋፍ ይበልጥ አጠናክረው መቀጠላቸውን የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሃደ ሲንቄዎች ገለጹ።

በኢትዮጵያ ለዘመናት በምክንያትነት የሚነሱ መሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በምክክር አማካኝነት የጋራ መግባባት ለመፍጠርና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ መቋቋሙ ይታወሳል። 

ኮሚሽኑ በሀገሪቱ ታሪክ አሳታፊ፣ ግልጽና ታማኝ የሆነ የምክክር መድረክ ለማዘጋጀት ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር የባለድርሻ አካላት መለየትና አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራዎችን በየደረጃው ሲያከናውን ቆይቷል።

ኮሚሽኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሀገራዊ የምክክር ጉባዔውን ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ለማካሄድ መዘጋጀቱ ይታወቃል።

በመሆኑም መላ ኢትዮጵያዊያን ለዚህ ታሪካዊ ሁነት መሳካት ከኮሚሽኑ ጎን በመሆን የሚጠበቅባቸውን መወጣት እንዳለባቸው ኮሚሽኑ ከወዲሁ ጥሪ አቅርቧል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞንና በሮቤ ከተማ የሚገኙ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሃደ ሲንቄዎች ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ ሀገራዊ የምክክር መድረኩ በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ ቂምና ቁርሾዎችን በዘላቂነት ፈትቶ የህዝቦችን አንድነት ለማጠናከር ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረውም አንስተዋል።

በባሌ ዞን የሀገር ሽማግሌ አቶ ታምሩ ደገፋ እንደገለጹት፤ ሀገራዊ ምክክሩ የሁሉንም ሀሳብ በመቀበል መሰረታዊና ወሳኝ ጉዳዮች ላይ መግባባትን ይፈጥራል የሚል ታላቅ ተስፋ ጥለውበታል። 

እንደ ሀገር የማያግባቡና ዘመናትን ያስቆጠሩ መሰረታዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትና ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ግብ ይዞ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው የኮሚሽኑ ጥረት እንዲሳካ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ያደርጋሉ።


 

ሌላው አስተያየት ሰጪ ሼህ ሙባረክ ሐጅ አብዱልአዚዝ በበኩላቸው፤ በአካባቢው ያሉትን ሀገር በቀል የሰላም እሴቶች እና ባህላዊና ሃይማኖታዊ የግጭት መፍቻ እውቀቶችን በማጋራት ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የበኩላቸውን እያበረከቱ መሆኑን ገልጸዋል። 

የኮሚሽኑ የእስካሁኑ ሂደት የሀሳብ ፍትሃዊነትና አካታችነት የሰፈነበት መሆኑን ያነሱት ሼህ ሙባረክ፤ ለኮሚሽኑ ስራ ውጤታማነት የሁሉም ወገን የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ፣ ይሄንን እውነታ ለህብረተሰቡ የማስገንዘብ ሥራችንን አጠናክረን ቀጥለናል ብለዋል።


 

በአዳማ ከተማ በተካሄደው መድረክ ላይ የመሳተፍ ዕድል ያገኙት የሃይማኖት አባት ፓስተር ሐብታሙ ካሳ፤ ሀገራዊ ምክክሩ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል የሚስተዋሉ ችግሮችን በውይይት ፈትቶ አብሮነትን ለማጠናከር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አብራርተዋል። 

ምክክሩ በተለይም በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀትና ሀገርን ወደ እድገት ጎዳና ለማሻገር መሠረት ስለሚጥል፣ ለተግባራዊነቱ ህብረተሰቡን የማስተማርና ግንዛቤ የመፍጠር ተግባር እያከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

ሃደ ሲንቄ መኮ ሐሰን በበኩላቸው፤ በሀገራችን ኢትዮጵያ በግለሰቦችና በማህበረሰብ መካከል አለመግባባትና ቁርሾዎች ሲኖሩ ተመካክሮ የሚፈታበት ሰፊ ሀገር በቀል እውቀትና ዕሴት እንዳለ አስታውሰዋል። 

ሀገራዊ የምክክር መድረኩም ይህንኑ በጎ ዓላማ የሚያጎለብት፣ ሀገርን በእርቅ በማሻገር ልማትን የሚያፋጥንና የህዝቦችን አንድነት የሚያጠናክር መሆኑን በመረዳት ለስኬታማነቱ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም