በክልሉ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት እየተመዘገበባቸው ነው - ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት እየተመዘገበባቸው ነው - ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ
ሐረር፤ ሰኔ 11/2018(ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት እየተመዘገበባቸው መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።
በሐረሪ ክልል የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና መሰጠት ተጀምሯል።
የሐረሪ ክልል በአዲሱ የፈተና ሥርዓት የተማሪዎችን የማሳለፍ ምጣኔ እና አጠቃላይ የውጤት ጥራት ለማሳደግ ልዩ ልዩ የማጠናከሪያ ትምህርቶችንና የክለሳ ፕሮግራሞችን ሲተገብር ቆይቷል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በክልሉ እየተሰጠ የሚገኘውን የ8ኛ ክፍል ፈተና ዛሬ ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት በክልሉ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።
በተከናወኑ ተግባራትም የተሻሉ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸው፤ በክልሉ እየታየ የሚገኘው የትምህርት ተሳትፎ፣ ጥራትና የተማሪ ውጤት የማጎልበት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ጌቱ ነገዎ በበኩላቸው ለፈተናው አስፈላጊው ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል ብለዋል።
በክልሉ በአጠቃላይ በገጠርና በከተማ 30 የፈተና ጣቢያዎች የተዘጋጁ ሲሆን 4ሺህ 614 ተማሪዎች ፈተናውን እየወሰዱ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
ትምህርት ቢሮው ተማሪዎችን ለፈተና ለማብቃትና ውጤትን ለማሻሻል በትኩረት ሲሰራ መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡
በተለይም ተማሪዎችን ለፈተና ለማብቃት በትምህርት ቤቶች የማጠናከሪያ ትምህርትና ሞዴል ፈተና አዘጋጅቶ የመስጠትና ሌሎች ተግባራት ሲከናወኑ መቆታቸውን አስታውሰዋል፡፡