ቀጥታ፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተማሪዎች ተከታታይነት ያለው የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲያገኙ በማድረግ ውጤታማ እንዲሆኑ ተሰርቷል

አሶሳ፤ ሰኔ 11/2018 (ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተማሪዎች ተከታታይነት ያለው የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲያገኙ በማድረግ ውጤታማ እንዲሆኑ መሠራቱን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና መሰጠት መጀመሩን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል።

በሀገሪቱ የተጀመረውን የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ሪፎርም ተከትሎ፣ የብሔራዊና የክልላዊ ፈተናዎች አሰጣጥ ሥርዓት ጥብቅና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን መደረጉ ይታወሳል።

ይህንን አዲስ የፈተና ሥርዓት ተማሪዎች በብቃት መወጣት እንዲችሉ፣ መደበኛውን የመማር-ማስተማር ሂደት ከማጠናከር ባለፈ ቅዳሜና እሁድን ጨምሮ ከትምህርት ሰዓታት ውጭ ተከታታይነት ያላቸው የክለሳና የማጠናከሪያ ፕሮግራሞችን መስጠት የክልሎች ዋነኛ ስትራቴጂ ሆኖ እየተገበረ ይገኛል።


 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ትምህርት ቢሮም ካለፉት ዓመታት ጀምሮ ፍትሐዊና ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ለማድረስ በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱ ተገልጿል።

በተለይም ተማሪዎች በተለያዩ ማኅበራዊና አካባቢያዊ ምክንያቶች ሊያመልጧቸው የሚችሉ ትምህርቶችን ለማካካስና በተለይም የ6ኛ፣ የ8ኛ እና የ12ኛ ክፍል ተፈታኞችን ውጤታማነት ለማሳደግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሠራ መቆየቱን ገልጿል።

የቢሮው የስርዓተ ትምህርት እና ተቋማት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ሙሐመድ ኡስማን ዛሬ በአቡራሞ 1ኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተው ፈተናውን ሲያስጀምሩ እንዳሉት፤ ተማሪዎች ተከታታይነት ያለው የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲያገኙ በማድረግ ውጤታማ እንዲሆኑ ተሰርቷል።

በተለይም ቢሮው በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለፈተናው ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ጠቅሰው፥ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ ሰፋፊ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።

ተማሪዎች ፈተናውን በተረጋጋ ሁኔታ እንዲፈተኑ አስፈላጊውን የስነ ልቦና እና ምክር እንደተሰጣቸውም ተናግረዋል።

በዘንድሮው ዓመት በክልሉ በ313 ትምህርት ቤቶች ላይ ከ21 ሺህ በላይ የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተና እየወሰዱ ይገኛሉ ብለዋል።

በዘንድሮው የትምህርት ዘመን የ8ኛ እና የ6ኛ ክፍል የፈተና የእርማት ማሽን ግዢ በመፈጸሙ የፈተናውን ውጤት በአጭር ጊዜ ውስጥ በማሳወቅ ተማሪዎች ለቀጣይ የትምህርት ጊዜ ዝግጁ እንዲሆኑ ይደረጋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም