ቀጥታ፡

ተማሪዎችን ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ ማብቃት የተሻለ ትውልድ ለመገንባት ያግዛል

ጅግጅጋ፤ ሰኔ 11/2018(ኢዜአ)፦ ተማሪዎችን ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ በተሻለ የትምህርት ጥራት ማብቃት ሀገር ገንቢ ትውልድ ለመገንባት ያግዛል ሲሉ የሶማሌ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ ጉሌድ አህመድ አሊ ገለጹ።

በሶማሌ ክልል የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና መሰጠት ተጀምሯል።

በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና ብቁ ዜጋ ለማፍራት ሰፊ የሪፎርም ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በተለይም የታችኛው የትምህርት እርከን ለተማሪዎች ቀጣይ የዕውቀት አድማስና ለተተኪው ትውልድ ሰብዕና ግንባታ ወሳኝ መሠረት በመሆኑ፣ አጠቃላይ የትምህርት ጥራቱ ትኩረት ተሰጥቶት ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።

የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ከሚከናወኑ ቁልፍ ተግባራት መካከል ደግሞ ተማሪዎች በራስ መተማመናቸውን አሳድገው፣ ፈተናን በራሳቸው አቅም በመስራት የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ማስቻል ዋነኛው ነው።


 

ዛሬ በተጀመረው የሶማሌ ክልል የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተናም ተማሪዎች በራሳቸው በመተማመን የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ መሰራቱ ነው የተገለጸው።

ፈተናውን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢብራሂም ዑስማን እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ መሀመድ ሼክ አደን በሼክ አብዱሰላም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተው በይፋ አስጀምረዋል።

የሶማሌ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ ጉሌድ አህመድ አሊ በወቅቱ እንዳሉት፤ ተማሪዎችን ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ በተሻለ የትምህርት ጥራት ማብቃት ሀገር ገንቢ ትውልድ ለመገንባት ያግዛል።

ዛሬ በተጀመረው ክልል አቀፍ የ8ኛ ክፍል ፈተናን 29 ሺህ 631 ተማሪዎች እንደሚወስዱ ገልጸው፤ ፈተናው በክልሉ 704 ትምህርት ቤቶችና በ113 የፈተና ጣቢያዎች እየተሠጠ ነው ብለዋል።

የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተናው ከሰኔ 11 ጀምሮ እስከ ሰኔ 12 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚሰጥም እንዲሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም