የኢትዮጵያን አስደናቂ የአረንጓዴ ዐሻራና የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ሊተገብሩት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን አስደናቂ የአረንጓዴ ዐሻራና የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ሊተገብሩት ይገባል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ተሞክሮ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ሊሰፋ እንደሚገባ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ኦፊሰር ቻርለስ አኮል ገለጹ።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የአካባቢ መራቆትን ለመግታትና የውሃ ሃብት ዘላቂነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ተጨባጭ ውጤቶች እያመጣ መሆኑን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ ባደረጉት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር እስካሁን ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተመሳሳይ የ2018 የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብርን በይፋ ያስጀመሩ ሲሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ 8 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ግብ መጣሉን አስታውቀዋል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ኦፊሰር ቻርለስ አኮል ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር የተጎዱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ እያደረገ የሚገኝ ኢኒሼቲቭ ነው።
በዘላቂ ውሃ አጠቃቀም ላይም መርሃ ግብሩ ትርጉም ያለው ውጤት እያመጣ መሆኑን ተመልክተናል ያሉት ኦፊሰሩ፤ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራና አካባቢ ጥበቃ ላይ የሚደነቅ ሥራ እያከናወነች ነው ብለዋል።
የደን ሽፋንን ማሳደግ የውኃ ሀብትን በዘላቂነት ለመጠበቅ ተጨባጭ ማሳያ መሆኑን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ የደን ሽፋንን ለማሳደግ ፈጣንና ሁሉን አቀፍ ሥራዎች እየተገበረች መሆኑን ተመልክቻለሁ ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ ተሞክሮን ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሊተገበሩት እንደሚገባ ጠቁመው፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ተሞክሮ ወደ ሌሎች ሀገራት እንዲሰፋ እያደረጉት ያለውንም ጥረት አድንቀዋል።
በአፍሪካ የአካባቢ ጥበቃን ለማሳለጥ “ታላቁ የአፍሪካ አረንጓዴ ግንብ” የተሰኘ መርሃ ግብር መኖሩን አስታውሰው፤ ይህን መርሃ ግብር ከኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ጋር ማቀናጀት ለአህጉራዊ አካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው ብለዋል።
የአረንጓዴ ልማቱን ማስፋፋት በአፍሪካ ያለውን የውሃና የመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ከማሻሻሉ በላይ ለስራ እድል ፈጠራና ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው አስረድተዋል።