የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፈው ለመስጠትና የሕዝብን ሰላም ለማናጋት የሚጥሩ አካላትን መታገል የጋራ ሃላፊነታችን ነው - የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፈው ለመስጠትና የሕዝብን ሰላም ለማናጋት የሚጥሩ አካላትን መታገል የጋራ ሃላፊነታችን ነው - የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች
ሀዋሳ፤ ሰኔ 11/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፈው ለመስጠትና የሕዝብን ሰላም ለማናጋት የሚጥሩ አካላትን መታገል የጋራ ሃላፊነታችን ነው ሲሉ በሲዳማ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።
በሲዳማ ክልል የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገር ብሄራዊ ጥቅም፣ ሰላምና ልማት ላይ ያላቸውን አቋምና ምልከታ በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በቆይታቸውም የሀገር ሰላምና ልማትን ማደናቀፍ፣ ከብሄራዊ ጥቅም በተቃራኒ መቆም በየትኛውም መመዘኛ ትክክል ያልሆነ ተግባር መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፈው ለመስጠትና የሕዝብን ሰላም ለማናጋት የሚጥሩ ባንዳዎችን መታገል የጋራ ሃላፊነታችን ነው ብለዋል።
የሲዳማ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢና የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራሲ ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ በለጠ ሲጌቦ፤ በሀገር ብሔራዊ ጥቅም፣ ሰላምና ልማት ላይ ያለልዩነት የምንሰራበት የጋራ አጀንዳችንና ሀገራዊ ግዴታችን ጭምር ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ለዘላቂ ልማትና ጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ተቀራርበንና ተደጋግፈን ለመስራት ተዘጋጅተናል ነው ያሉት።
በሀሳብ የበላይነት በሰላማዊ መንገድ መታገል የማይፈልጉ እንዲሁም በባንዳነት የተሰለፉ አካላት በየትኛውም መመዘኛ ታሪካዊ ስህተት እየፈፀሙ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፈው ለመስጠትና ሰላምን ለማናጋት የሚጥሩ አካላትን መታገል የጋራ ሀገራዊ ሃላፊነታችን በመሆኑ በቁርጠኝነት እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ ሥራ አስፈጻሚና በክልሉ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ተወካይ ወይዘሮ ሃረገወይን ዘሪሁን፤ የሰላምና የልማት ጉዳይ ለማንም የማይተው የሁላችንም ቋሚ አጀንዳ ነው ብለዋል።
በመሆኑም የህዝብን ሰላምና ልማት በማደናቀፍ ሀገርን ለማፍረስ የሚጥሩ ጸረ ሰላም ሃይሎችን ድርጊት በመታገል በኢትዮጵያ ጠንካራ ሀገረ መንግስት የመገንባት ሃላፊነታችንን ለመወጣት እንሰራለን ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ የብዝሃ እምነትና ባህል ሀገር መሆኗን አስታውሰው፣ ሁልጊዜም ልዩነቶችን በነባር ባህሎችና በምክክር በመፍታት ጠንካራ መንግስትና ሃገር መገንባት ይገባናል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለመጉዳትና ሰላሟን ለማናጋት የሚደረግ ጥረት ክህደት ስለመሆኑ አንስተው ከምንም በማስቀደም ለሀገር መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) ሊቀመንበር ለገሰ ላንቃሞ በበኩላቸው፤ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም፣ ሰላምና ልማት አጠናክሮ ማስቀጠል የፓርቲያችን የማይናወጥ አቋም ነው ብለዋል።
የውጭ ባዳዎችንና የውስጥ ባንዳዎችን የጥፋት አጀንዳ ተቀብለው ልዩነቶችን በሃይል ለመፍታት እየተንቀሳቀሱ ያሉ ጸረ ሰላም ሃይሎችን እንደሚታገሉ ገልጸው፣ በሀገር ብሔራዊ ጥቅም ላይ ልዩነት የለንም ብለዋል።
ለዘመናት ሳያግባቡን የቆዩ ሀገራዊ ጉዳዮችን ለመፍታት ታሪካዊ እድል የሰጠንን ሀገራዊ ምክክር በመጠቀም ችግሮችን በምክክር በዘላቂነት መፍታትና ሀገርን ማጽናት አለብን ሲሉም ገልጸዋል።