7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ቅቡልነት ያለው መንግሥትና ጠንካራ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት መሠረት የጣለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ቅቡልነት ያለው መንግሥትና ጠንካራ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት መሠረት የጣለ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2018(ኢዜአ)፦ ሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ቅቡልነት ያለው መንግሥትና ጠንካራ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት መሠረት የጣለ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን ገለጹ።
ኢትዮጵያ ከ54 ሚሊየን በላይ ዜጎች ድምጻቸውን ለመስጠት የተመዘገቡበትንና 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳተፉበትን 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በስኬት አካሂዳለች።
ዜጎች በየምርጫ ጣቢያቸው ከማለዳ 12 ሰዓት እስከ እኩለ ሌሊት በነቂስ በመውጣት ድምጻቸውን ሰጥተዋል፡፡
የምርጫ ሒደቱን በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን እንደገለጹት፥ ምርጫው የበርካታ ፓርቲዎች ፉክክር የታየበትና በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ መጠናቀቁም በሀገሪቱ የሰከነ የፖለቲካ ባህል እየተገነባ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።
ይህ ዓይነቱ አካሄድ በቀጣይ ለሚመሰረተው መንግስት ጠንካራ ሕዝባዊ ቅቡልነት ከመስጠቱ በላይ፣ ለተረጋጋ የፖለቲካ ሂደትና ለልማት ዋነኛ መሠረት ይሆናል ብለዋል።
በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ጌትዬ ትርፌ (ዶ/ር)፥ የምርጫ ሂደቱ ከዚህ በፊት ከተካሄዱ ምርጫዎች እጅግ የተሻለ ዴሞክራሲያዊነት የታየበት መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ህብረተሰቡ ሀገርን በማስቀደም ከቅድመ ምርጫው እስከ ድህረ ምርጫ ድረስ ያሳዩት ኃላፊነት የተሞላበት እንቅስቃሴ የሚደነቅ ነው ብለዋል።
በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት መገናኛ ብዙኃን ያለምንም ልዩነት ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ለማሳተፍ የነበራቸው ቁርጠኝነትም ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ጠቅሰዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሕዝቡ የሰከነ እንቅስቃሴ ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ማስቻሉንም በመግለጽ፡፡
በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የፖሊሲና ስትራቴጂ ተመራማሪ ተመስገን ዋለልኝ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የዘንድሮው ምርጫ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ ድምጹን የሰጠበት፣ ለዴሞክራሲ ባህል መዳበር ያለውን ቁርጠኝነትም በጽናቱ ያረጋገጠበት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ መብቱን የመጠቀምና የመጠበቅ ብስለቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ያሳየ ምርጫ እንደሆነም አንስተዋል።
በዚህ ምርጫ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል እጩዎች ያለምንም ጫና የመወዳደር፣ ሀሳባቸውን በነጻነት የማንጸባረቅና አማራጭ ፖሊሲዎቻቸውን ለሕዝብ የማቅረብ እድል ማግኘታቸውንም ጠቅሰዋል።
ምርጫው በአሳታፊነቱ፣ በፍትሐዊነቱና በተፈጠሩ ምቹ የመወዳደሪያ ምህዳሮች በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ወደ ተሻለ የዴሞክራሲ ምዕራፍ ሽግግር የተደረገበት መሆኑን ገልጸዋል።
የአፍሪካ ህብረትና የኢጋድ የታዛቢዎች ልዑክ ቡድን ከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ የታየበት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ መጠናቀቁን ማረጋገጣቸውን መግለጻቸው ይታወቃል።