ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ አመካካሪዎች የግንዛቤና የክህሎት ሥልጠና መስጠት ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ አመካካሪዎች የግንዛቤና የክህሎት ሥልጠና መስጠት ተጀመረ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ አመካካሪዎች ያዘጋጀው የግንዛቤና የክህሎት ሥልጠና መስጠት ጀምሯል።
በአዲስ አበባ እየተሰጠ የሚገኘው ይህ የአመካካሪዎች ሥልጠና ከዛሬ ሰኔ 11 እስከ 17 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ለሰባት ቀናት እንደሚቆይ ተመላክቷል።
በሥልጠናው መክፈቻ ላይ የተገኙት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እንደገለጹት፤ ይህ የሥልጠና መርሃ ግብር ልዩነቶች በምክክር የሚፈቱበት፣ በግልጽነትና በመግባባት የሚቀረፉባት ኢትዮጵያን ለመገንባት በጋራ በሚደረገው ጉዞ ላይ ሌላ አንድ ትልቅ ምዕራፍና ስኬት ነው።
አመካካሪዎች ይህን ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት በታማኝነት የሚሸከሙ ባለአደራዎች መሆናቸውን ጠቅሰውም፤ ራሳቸውን የሀገሪቱን ማህበራዊ፣ ሕዝባዊና ዴሞክራሲያዊ መጻኢ ዕድል በጋራ የሚገነቡ ታሪክ ሰሪዎች አድርገው ማየት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
ይህ ሥልጠና አመካካሪዎች የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ክብር የሚጠብቁ እንዲሁም ለሰላም፣ ለፍትህና ለአንድነት ያላቸውን የጋራ ምኞት የሚያሳኩ ምክክሮችን መምራት የሚያስችላቸውን እውቀት፣ ክህሎትና እሴት መጨበጥ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
አመካካሪዎች በጉባኤው ወቅት ሁሉም ተሳታፊዎች እኩል የመናገርና የመሳተፍ ዕድል እንዳላቸው ማረጋገጥ፣ በውይይት ወቅት የሚነሱ አለመግባባቶችን በአግባቡ መምራት እንዲሁም ውይይቱ ወደ ጋራ መግባባት እንዲያመራ መንገድ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡
አመካካሪዎች ይህንን ትልቅ ሀገራዊ አደራ በትሕትና፣ በገለልተኝነት እና በትዕግሥት እንዲወጡትም አደራ ብለዋል።