ቀጥታ፡

በመዲናዋ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ለፍራፍሬ ችግኞች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2018(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ለዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የፍራፍሬ ተክሎችን በስፋት ያካተቱ አምስት ሚሊየን ችግኞች መዘጋጀታቸውን የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ኃላፊ ግርማ ሰይፉ ገለጹ።

ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ በተከታታይ ባከናወነችው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር እስካሁን 48 ቢሊየን ችግኞችን መትከል ችላለች።


 

የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትና ብልጽግና ለማረጋገጥ ከሀገራዊ ሕልሟ ጋር የተቆራኘ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበበት ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር በቢሾፍቱ በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት፣ በዘንድሮው ዓመት ብቻ ስምንት ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ግብ ተቀምጧል።

አባቶቻችን በአድዋ ላይ ታሪካዊ ገድል ፈጽመው ሀገር እንዳስረከቡን ሁሉ፣ የአሁኑ ትውልድም በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር ሌላኛውን የአረንጓዴ አርበኝነት ገድል እየደገመ ይገኛል።

ይህ ታላቅ ሀገራዊ ንቅናቄ የሚፈጥረው የአየር ንብረት ለውጥ የመቋቋም አቅምና የምግብ ሉዓላዊነት ስኬት፣ ለቀጣዩ ትውልድ ሉዓላዊነቷ የተረጋገጠና የበለጸገች ሀገር ለማስረከብ ለተጀመረው ጉዞ እንደ ትልቅ ምሰሶ የሚቆጠር ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ የውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ኃላፊ ግርማ ሰይፉ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በመዲናዋ ዘንድሮ ለሚከናወነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር የዝግጅት ሥራ ተጠናቋል።

በአሁኑ ወቅትም የችግኝ ማፍላትና የቦታ መረጣ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው የጉድጓድ ቁፋሮ ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በከተማዋ ከዚህ ቀደም የተተከሉ ችግኞች የፅድቀት ምጣኔ በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑን ጠቁመው፣ በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር የፍራፍሬ ችግኞችን በስፋት ያካተቱ አምስት ሚሊየን ችግኞች እንደሚተከሉ አስታውቀዋል።

በመሆኑም ወጣቶች እና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በዘንድሮው የችግኝ ተከላና እንክብካቤ ሥራ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።


 

በሱሱኒ ችግኝ ጣቢያ የዘር ብዜትና የችግኝ እንክብካቤ ባለሙያ ተሾመ ፉፋ እንደገለጹት በጣቢያው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርን ስኬታማ ለማድረግ ከፍተኛ ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል፡፡

ይህንንም ተከትሎ በጣቢያው አንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ችግኞች ለተከላ ዝግጁ የተደረጉ ሲሆን በርካታ የተዳቀሉ የፍራፍሬ ዘር ችግኞች መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።

ችግኞቹ ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ ተከታታይ ክትትልና እንክብካቤ እንደሚያስፈልጋቸው የተናገሩት ደግሞ ሌላኛዋ ባለሙያ የሆኑት ፅጌ ነጋ ናቸው።


 

አረንጓዴ ዐሻራን ከግብ ለማድረስ ችግኝን መትከል ብቻ ሳይሆን ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግም ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም