የኮሪደር ልማቱ የድሬዳዋን የተደበቀ ውበት በመግለጽ ከተማዋን ተመራጭ የስራና የመኖሪያ ማዕከል አድርጓታል - ኢዜአ አማርኛ
የኮሪደር ልማቱ የድሬዳዋን የተደበቀ ውበት በመግለጽ ከተማዋን ተመራጭ የስራና የመኖሪያ ማዕከል አድርጓታል
ድሬዳዋ፤ ሰኔ 11/2018(ኢዜአ)፦ የኮሪደር ልማቱ ታሪካዊ ቅርሶችን በጠበቀ መልኩ መከናወኑ ድሬዳዋን ተመራጭ የኢንቨስትመንትና የቱሪስት መዳረሻ እያደረጋት መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የከተማዋ አመራሮችና ነዋሪዎች ገለጹ።
በድሬዳዋ ከተማ የሚገኙ ጥንታዊ ህንጻዎች፣ ልዩ የሥነ-ህንጻ ጥበብ እና የህዝቦቿ የባህል ብዝሃነት የቱሪስት መስህብ ሆነው መቆየታቸው ይታወቃል።
በአሁኑ ወቅት በመንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በሀገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች እየተተገበረ የሚገኘው የኮሪደር ልማት፣ የከተማዋን ገጽታ በማዘመን፣ መንገዶቿን በማስፋትና ለነዋሪዎች ምቹ አካባቢን በመፍጠር ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ ነው።
የኮሪደር ልማቱ የድሬዳዋን ታሪካዊ ማንነት ጠብቆ ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ዘርፍ አዲስ መነቃቃትን እየፈጠረ መሆኑን የአካባቢው አመራሮችና ነዋሪዎች ገልጸዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር በፕሮጀክት ፅህፈት ቤት የኮሪደር ልማት አስተባባሪ ወንድወሰን ጀንበሬ እንደተናገሩት፤ በአምስት አቅጣጫዎች የተከናወነው የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገፅታና ውበት አጉልቶ አውጥቷል።
በተለይም የከተማዋን ታሪካዊ ቅርሶችና ሃብቶች በጠበቀ መልኩ መከናወኑ ከተማዋን ዘመናዊ የኑሮና የስራ ተመራጭ ማዕከል እያደረጋት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በኮሪደር ልማቱ የተካተቱት ዘመናዊ መንገዶች፤ የመዝናኛ ማዕከላትና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ድሬዳዋን ይበልጥ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እያደረጋት ይገኛልም ብለዋል።
የአስተዳደሩ ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ነኢማ ኢብራሂም በበኩላቸው፤ የኮሪደር ልማቱ የቱሪዝም መዳረሻ የሆኑትን ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ሃብቶች ይበልጥ ማጉላቱን ገልጸዋል።
በተለይም ለድሬዳዋ ከተማነት መሠረት በጣለውና የቱሪስት መዳረሻነት እያገለገለ በሚገኘው ታሪካዊ የባቡር ጣቢያ ጋር ተዋህዶ የተሰራው ልማት ቅርሱን ቱሪስቶች ይበልጥ እንዲጎበኙት እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት።
ከቱሪዝም መዳረሻዎች ባሻገር የነዋሪውን ትስስርና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲጠናከር ምቹ መደላድል መፍጠሩን በመጠቆም።
ሌላው አስተያየት ሰጭ ሼህ አብዶ ኡመር፤ የኮሪደር ልማቱ የተደበቀውን የድሬዳዋን ውበትና ገፅታ በመግለጽ ነዋሪውን ያስደሰተ መሠረታዊ ስራ መሆኑን ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማቱ የድሬዳዋን የአስፋልት፣ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገዶችን ማስፋቱ የትራፊክ መጨናነቅና አደጋን በመቀነስ በኩል መሠረታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው ነዋሪ አቶ ሀብታሙ አሰፋ ናቸው።
በተለይም የተፈጠሩት የመዝናኛና የአረንጓዴ ቦታዎች ለአረጋውያንና ለልጆች መዝናኛ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠና ማህበራዊ መስተጋብርን እንደሚያዳብር አንስተዋል።
የከተማ አስተዳደሩ እያከናወናቸው ካሉ የኮሪደር ልማት ስራዎች በተጓዳኝ የግል ተቋማትም ከተማዋን በማደስና በማስዋብ በኩል ከአንድ ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ማድረጋቸውን ከአስተዳደሩ የፕሮጀክት እና የኮሪደር ልማት ፅህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።