በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን የፍራፍሬ ልማትን በማስፋፋት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን የፍራፍሬ ልማትን በማስፋፋት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው
ጊምቢ፤ ሰኔ 11/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ከቡና ልማት ጎን ለጎን የፍራፍሬ ልማትን በማስፋፋት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
በዞኑ በበጀት ዓመቱ ከ2 ነጥብ 3 ሚሊየን ኩንታል በላይ የፍራፍሬ ምርት መሰብሰቡም ተመላክቷል።
በጽሕፈት ቤቱ የፍራፍሬ ልማት ባለሙያ ጂብሪል መንጌ እንዳስታወቁት፤ ዞኑ በስፋት ከሚታወቅበት የቡና ልማት ጎን ለጎን በፍራፍሬ ልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተግባራዊ የተደረገው የፍራፍሬ ልማትም የአርሶ አደሩን የሥራ ባህል በመቀየር በኩል አበረታች ውጤት ማስገኘቱን ተናግረዋል።
ልማቱ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የምግብ ሥርዓትን ከማሻሻል አንጻር የላቀ ሚና እንዳለው ጠቁመው፤ ይህንን ታሳቢ ያደረገ እንቅስቃሴ በየደረጃው ሲካሄድ መቆየቱን አውስተዋል።
በአሁኑ ወቅት 41 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት የፍራፍሬ ምርት መስጠት በሚችልበት ደረጃ ላይ የደረሰ ሲሆን፣ ከዚህም 2 ሚሊየን 399 ሺህ 710 ኩንታል የፍራፍሬ ምርት ተሰብስቦ ለገበያ ቀርቧል ብለዋል።
ለገበያ ከቀረቡት የፍራፍሬ ምርቶች መካከል አናናስ፣ ሙዝ፣ ማንጎ፣ አቮካዶ፣ ፓፓያና ብርቱካን ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ገልጸው፤ የተሻሻለ የአቮካዶ ዝርያ ምርት ለውጭ ገበያ የሚቀርብ በመሆኑ፣ የአካባቢው አርሶ አደሮች ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱንም ተናግረዋል።
በዚህ ዓመትም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማሳደግ፤ ልማቱን ከአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ጋር በማቀናጀት የፍራፍሬ ችግኞችን በብዛትና በጥራት ለተከላ እየተዘጋጀ መሆኑን።
የልማቱ ተሳታፊ የሆኑት የላሎ አሳቢ ወረዳ አርሶ አደር ታረቀ ጂሬኛ፤ ከዚህ ቀደም ሕይወታቸውንና ገቢያቸውን በቡና ልማት ላይ ብቻ መስርተው እንደነበር አስታውሰዋል።
ሆኖም መንግሥት ያመቻቸላቸውን የፍራፍሬ ችግኝና ምርጥ ዘር በመጠቀም በዘርፉ መሰማራታቸውንና ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በይዞታቸው ላይ ሙዝ፣ አቮካዶ እና አናናስ በማልማት በዓመት የተሻለ ገቢ እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላው የሆማ ወረዳ አርሶ አደር ገረመው ጂሩ በበኩላቸው፤ ከግብርና ምርምር ማዕከል የወጣ የተሻሻለ የሙዝ ዝርያን በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ምርቱን ለአካባቢው ገበያ በማቅረብ በአንድ ዙር እስከ 30 ሺህ ብር ገቢ እያገኙ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ልማቱን በማጠናከር አቮካዶና ሙዝ በስፋት ለማልማት ማቀዳቸውን አስታውቀዋል።