በክልሉ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የደን ሃብት ሽፋንን ከማሳደግ ባለፈ የከርሰና ገጸ ምድር ውሃ መጠን እንዲጨምር አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የደን ሃብት ሽፋንን ከማሳደግ ባለፈ የከርሰና ገጸ ምድር ውሃ መጠን እንዲጨምር አስችሏል
ባህር ዳር፤ ሰኔ 11/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የደን ሃብት ሽፋንን ከማሳደግ ባለፈ የከርሰና ገጸ ምድር ውሃ መጠን በመጨመር የመስኖ ልማትን ለማሳደግ ማገዙን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለፀ።
የቢሮው ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ መሰሉ ብርሃኑ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በክልሉ ህብረተሰቡን በማሳተፍ የተከናወኑ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ትግበራ የደን ሃብት ሽፋኑን ከማሻሻል በተጨባጭ የአፈር መከላትን መከላከል አስችሏል።
እንዲሁም የክልሉን የደን ሃብት ሽፋን ከ14 ነጥብ 6 በመቶ ወደ 18 ነጥብ 9 በመቶ ማሳደግና የከርሰ ምድርና ገፀ ምድር ውሃ ሀብትን በማሳደግ የመስኖ ልማትን ለማሳደግ ማገዙን ጠቁመዋል።
ዘንድሮም ተግባሩን በማስቀጠል የክረምት ወቅት የፍራፍሬ፣ የውበት፣ የደንና ሌሎች ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።
ችግኝ ተከላውን በ261 ሺህ 460 ሄክታር መሬት ላይ ለማከናወን የጉድጓድ ቁፋሮ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህ ዓመት ለሚከናወነው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ውጤታማነትም በየደረጃው የሚገኘው አመራር፣ ወጣቶችና ሴቶች ብሎም መላው ህብረተሰብ በባለቤትነት እንዲሳተፍም ጠይቀዋል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ሃላፊ የሰውዘር ደመላሽ በበኩላቸው በከተማው ለሚከናወነው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የሚተከሉ ችግኞች ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።
ችግኞቹን ለመትከል የቦታ ልየታን ጨምሮ የመትከያ ጉድጓድ ቁፋሮ መከናወኑን ገልፀው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ላላቸው፣ ለደን እና ለውበት የሚሆኑ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በችግኝ ማፍላት ለተሰማሩ ወጣቶች መልካም አጋጣሚ በመፍጠር በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉን የገለፀው ደግሞ በባህር ዳር ከተማ በችግኝ ማፍላት ስራ ላይ የተማራው ወጣት ንጉስ ቻሌ ነው።
ሦስት ሆነው በመደራጀት ችግኞችን አፍልተው ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሶ፤ በዚህ ዓመት ለሚከናወነው ችግኝ ተከላም 70 ሺህ ችግኞችን ማዘጋጀታቸውን ገልጿል።