በዓለም ዋንጫው አፍሪካዊቷ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከፖርቹጋል ጋር አቻ ተለያየች - ኢዜአ አማርኛ
በዓለም ዋንጫው አፍሪካዊቷ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከፖርቹጋል ጋር አቻ ተለያየች
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2018 (ኢዜአ):- በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የምድብ 11 የመጀመሪያ መርሐ ግብር ፖርቹጋል ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
ትናንት ማምሻውን በሂውስተን ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ጆአኦ ኔቬስ በስድስተኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል ፖርቹጋል መሪ ሆናለች።
የመጀመሪያው አጋማሽ ማብቂያ ላይ አሮን ዊሳ ከመረብ ላይ ያሳረፈው ጎል ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን አቻ አድርጓል።
ዊሳ ለኮንጎ በዓለም ዋንጫ ታሪክ የመጀመሪያውን ጎል በማስቆጠር ታሪክ ሰርቷል።
ፖርቹጋል ከፍተኛ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ብትወስድም ሁለቱ ቡድኖች ተቀራራቢ የግብ እድሎችን ፈጥረዋል።
ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ጎሏን ከማስቆጠር ባለፈ የመጀመሪያ ነጥቧንም አግኝታለች።
አፍሪካዊቷ ሀገር ከ52 ዓመታት በኋላ ወደ ዓለም ዋንጫው መመለሷ ይታወቃል።
የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ፍሊክስ ሼሲኬዲ በስታዲየሙ ተገኝተው ጨዋታውን በመከታተል ቡድኑን አበረታተዋል።
ዓለም ዋንጫውን ያነሳሉ ተብለው ግምት ከተሰጣቸው ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ፖርቹጋል ነጥብ ጥላለች።
ስድስተኛ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎውን ያደረገው አምበሉ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በ41 ዓመት ከ132 ቀናት በመጫወት በውድድሩ ታሪክ በአንጋፋው እድሜ የተሰለፈ ተጫዋች መሆን አዲስ ክብረ ወሰን አስመዝግቧል።